በእንተ ታሪክ

እስኪ ስለ ታሪክ የተነገሩ ሦስት አባባሎችን ላስታውሳችሁ፡፡

“ታሪክ ራሱን ይደግማል፡፡”
“ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችን ነው፡፡”
“ታሪክ ይገለበጣል፡፡”

ዛሬ የማካፍላችሁ ታሪክ የተገለበጠበትን አንድ ሁነት ነው፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና አቶ ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት” (1ኛ መጽሐፍ) በሚለው የታሪክ ድርሳናቸው ላይ የሚከተለውን ታሪክ በጥሩ አማርኛ አስፍረውት እናገኛለን፡፡
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ እነ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝና፣ አሜሪካና ኢጣሊያ ጦርነቱን አሸነፉ፡፡ ጀርመን፣ ኦስትሪያና ዩጎዝላቪያ ደግሞ ተሸነፉ፡፡ አሸናፊዎቹ በጀርመን ላይ የፈረዱባት ፍርድ የሚረሳ አይደለም፡፡ በተለይ በጀርመን ክፉኛ ቆስላ የነበረችው ፈረንሣይ ለጀርመን ምንም ርህራሄ አላሳየችም፡፡

(የዛሬን አያድርገውና እነዚህ ሁለቱ አገሮች ከድሮ ጀምሮ እርስ በርስ ሲበላሉ የኖሩ ሕዝቦች ነበሩ፡፡ ፍሬዴሪክ የተባለው የጀርመን ንጉሥ በአንድ ወቅት “የፈረንሳይ ወታደሮች ወንድ ይመስላሉ እንጅ ቢገልቧቸው ሴት ናቸው” ብሏቸው ነበር፡፡ ታሪክ ይገለበጥ የለ፣ በኋላ ፈረንሣዊው ንጉሥ ናጶሊዮን ተነስቶ ከባድ ክንዱን በጀርመንና በሌሎችም ላይ አሳረፈባቸው፡፡)

ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመልሳችሁ፡፡

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ፣ ኅዳር 11፣ 1918 እ.ኤ.አ ጀርመን የሽንፈትና የጦርነት ማቆም ስምምነት ከፈረንሣይ ጋር አደረገች፡፡ በኋላ ደግሞ ሰኔ 28፣ 1919 እ.እ.አ በቨርሳይል የተደረገው ስምምነት በጀርመን ላይ የሚከተሉትን ቅጣቶች አሳለፈ፡፡ ጀርመን፣

1. በሃይል የያዘቻቸውን የጎረቤት አገር ግዛቶች እንድትመልስ፣
2. በአፍሪካ፣ በፓሲፊክና በሩቅ ምሥራቅ የነበሯትን ቅኝ ግዛቶቿን ለአሸናፊዎች እንድታስረክብ፣
3. የምድር፣ የአየርና ባሕር ጦር ሃይል እንዳይኖራት፣
4. 132 ሚሊያርድ የወርቅ ማርክ የጦር ካሣ እንድትከፍል፡፡

(በተለይ የጦር ካሣው ጉዳይ ኢፍትሐዊ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ በርግጥ በፖለቲካ ውስጥ ፍትሕ የሚባል ነገር ጽንሰ-ሃሳቡም አይታወቅም፡፡ ፖለቲካ ጥቅም እንጅ ፍትሕ አይደለም፡፡ የምጣኔ ሃብት ሊቆቹ እንግሊዛዊው ካይነስ፣ አሜሪካውያኑ ዳውስና ያንግ ይህ ካሣ የሚከፈልበትን ሁኔታ እና መጠኑን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦችን አቅርበው ነበር፡፡)

ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ደግሞ ጥጋበኛዋን ጀርመን የሚመራው ዕብሪተኛው ሂትለር ጀመረው፡፡ መጀመሪያ የኦስትሪያንና የፖላንድን ሉአላዊነት በአጭር ቀናት ገፈፈች፡፡ ቀጥሎም ሂትለር ሉክሰምበርግ፣ ሆላንድና ቤልጄምን ተረማምዶባቸው ወደ ፈረንሣይ ገሠገሠ፡፡ ፈረንሣይ በአንድ ወር ውስጥ እንዳልሆነ ሆነች፤ ፓሪስ በአንድ ወር ውስጥ ተዋርዳ በናዚ መዳፍ ውስጥ ገባች፡፡ ክብሩን በውርደት የሸጠውና ወራዳው ማርሻል ፔተን ፈረንሣይ መሸነፏን የጦር ማቆሚያ ስምምነት ከናዚ ሂትለር ጋር በማድረግ ለሂትለር አስረከባት፡፡ እንግዲህ ከዚህ ላይ ነው ታሪክ ተገልብጦ የምናየው፡፡ ጀርመን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ኅዳር 11፣ 1918 እ.ኤ.አ ለፈረንሣይ በመንበርከክ የደረሰባትን ውርደትና የተጣለባትን አሳፋሪ ቅጣት ልትበቀል ነው፡፡

ወራዳው ማርሻል ፔተን ከሂትለር ጋር ያደረገው ጦርነት የማቆም ስምምነት የተደረገው ፓሪስ ከተያዘች በኋላ በስምንተኛው ቀን ሰኔ 22፣ 1940 እ.ኤ.አ ነው፡፡

ይህ ስምምነት የተደረገው ጀርመን በ1918 መሸነፏን ለፈረንሣይ አጎንብሳ በፈረመችበት የባቡር ፍርጎ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ፍርጎ ለ24 ዓመታት ያክል የፈረንሣይ ድል ምልክት ተደርጎ በሙዚም ውስጥ ተቀምጦ ነበር፡፡ አሁን ታሪክ ተገልብጦ፣ ሂትለር ይህን የባቡር ፍርጎ ከሙዚየሙ አውጥቶ ፈረንሳይ ጀርመን እግር ሥር ተንበርክካ መሸነፏን ፈረመችበት፡፡ ፈረንሣይ እስከዚያን ጊዜ ድረስ በታሪኳ እንዲህ ዓይነት ውርደት ደርሶባት አያውቅም ነበር፡፡

ምንጭ፡- ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት” (1ኛ መጽሐፍ)፣ 2005፣ ገጽ 320 – 321፣ 349 – 355

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s