ኑ! ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንከላከልለት!

የእሁድ፣ ግንቦት 29፣ 2009 ዓ.ም የሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ እንዳስነበበን ከሆነ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት “ኢ.ቢ.ሲ የቆመለትን ዓላማ የማይወክል፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት (የሥራ አስፈጻሚው አባላት) የሚታዘዝ ነው፤ የሕዝብ ሚዲያ መሆን አልቻለም፤ ዝግጅቶቹ አሰልቺ ናቸው፡፡” በማለት ብዙ ትችቶችን ሰንዝረው ኢቢሲን ደህና አድርገው ወቅጠው አስጥተውታል፡፡ (ግን እስከዛሬ የት ሄደው ነው?)

የምር ግን የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጨዋ ነው፤ ሁሉንም ወቀጣዎች አምኗል፤ ሽምጥጥ አድርጎ ቢክድ ምን ይመጣበት ነበር፡፡? ግፋ ቢል ከኢቢሲ ተነስቶ ወደ ሌላ መ/ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቢሆን ነው፡፡ ፓርላማውም ቢሆን ለዋና ሥራ አስፈጻሚው አድናቆቱን ችሯቸዋል፡፡ እሰይ፡፡ ማድነቅ መሰልጠን ነው፡፡

እና ኢቢሲ እንደዚያ ሲብጠለጠል ሳየው አንጀቴ አልችል አለ¡ ከትልፊፋት (መቶ ሚሊዮን) የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት አንድ ሰው ለኢቢሲ የሚቆም ይጠፋል? ፍትህ እንዲህ ስትበደልማ ዝም ማለት ደግም አይደል፡፡  ለዚህም ነው ለኢቢሲ ጥብቅና የቆምኩለት፡፡ በነገራችን ላይ ለኢቢሲ አለሁልህ ብሎ በቅድሚያ የቆመለት የሥጋ ወንድሙ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቻ ነው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሚያዝያ 29፣ 2009 ዓ.ም ዕትሙ “ኢ.ቢ.ሲን ለመውቀስ ሞራል ያለው ማን ነው?” በማለት በርዕሰ አንቀጹ ሽንጡን ገትሮ ተሟግቶለታል፡፡ እንዲህ ነው ወንድም ማለት፤ የክፉ ጊዜ ደራሽ፡፡ አቤት ዝምድናቸው ሲያስቀና፡፡

ከዚያ በፊት ግን አንድ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ኢቢሲን ግብ እንደሚሆን ኳስ ለባለሥልጣናት (ሥራ አስፈጻሚው) አመቻችቶ ያቀበለው ማን ነው? ፓርላማው አይደለምን?  ዋና ሥራ አስፈጻሚውን፣ የቦርድ አባሎቹን፣ መርጦ በፓርላማው የሚያስሾመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ (የመንግሥት ዋና ሥራ አስፈጻሚ) ነው ብሎ ሕግ አውጥቶ ለሥራ አስፈጻሚው ያቀበለው እኮ ፓርላማው ነው፡፡ የበጀቱን ጉዳይስ በከፊል የመንግሥት ተለጣፊ እንዲሆን ያደረገው ፓርላማው አይደለምን?

ባለሥልጣናቱ (ሥራ አስፈጻሚው) ደግሞ በሕግ ተደግፎ ተመቻችቶ የደረሰውን ኳስ በደንብ አድርጎ ከመረቡ ላይ አሳርፏል፡፡ የምር ግን ሥራ አስፈጻሚው ግን ተመቻችቶ የተሰጠውን ኳስ ባያገባ ኑሮ ማንም እየተነሳ ነበር የሚያብጠለጥለው፡፡ የሥራ አስፈጻሚውን ለግብ የሚሆን ኳስ ቢስተው ኖሮ፣ ኢቢሲ ራሱ በራሱ ሚዲያ በጧት፣ በአራት ሰዐት፣ በሰባት ሰዐት፣ ከምሽቱ ሁለት ሰዐት፣ ከምሽቱ አራት ሰዐት ላይ ባለው የስፖርት ዜናው ሲያብጠለጥለው ነበር የሚታይ፡፡ ጋዜጠኞቹም አሰልጣኙ ይነሳ ብለው ነበር የሚያውጁት፡፡ ኧረ እንኳንም አልሳተው፤ ሥራ አስፈጻሚው ሆይ እንዲህ ዓይነት ለግብ የሚሆኑ መልካም ዕድሎችን እንዳታበላሽ፤ ድፍን ኢትዮጵያ ነው ድጋፉን የሚነፍግህ፡፡

ምስኪን ኢቢሲ፣ እንደ ገና ዳቦ ከላይ (የፓርላማው) እና ከታች (የሥራ አስፈጻሚው) እሳት እየነደደባት ነው፡፡ ፓርላማው ለባለሥልጣናቱ (ሥራ አስፈጻሚው) አሳልፎ ሰጠው፤ ከታች ደግሞ ሥራ አስፈጻሚው እንደፈለገ ያሽከረክረዋል/ያዘዋል፡፡ ፓርላማው ኢቢሲ የቆመችበትን መሠረቷን ዘርጥጦ መቆሚያዋን አየር ላይ አደረገው፤ እናም ኢቢሲ በሰማይና በምድር መሃል ተንጠልጥላ ቀረች፡፡ ምን ብትበድል ነው ግን እንዲህ ዓይነት ፍርጃ? ወዮ! ኢቢሲን አያድርገኝ…

ለዚህም ነው ለኢቢሲ ለመከላከል ቆርጬ የተነሳሁት፡፡

ዶ/ር አንዳርጋቸው ጥሩነህ ”ወንበር” በምትባል በየመንፈቁ በምታተም የሕግ ቡለቲን 11ኛ መንፈቅ ዕትም በየካቲት 2005 ዓ.ም “The State Media in Ethiopia: Is it a Public Service Media?” የሚል መጣጥፍ (Article) ጽፈው ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፋቸው ውስጥ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ (4) እና (5) ጠቅሰው እንዳሰፈሩት ከሆነ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ ከመንግሥት ነጻ ሆኖ አገልግሎቱን እንዲያከናውን ሦስት መሠረታዊ ነገሮች መረጋገጥ አለባቸው ይላሉ፡፡

  1. ሚዲያው በፋይናንስ በኩል ከመንግሥት ነጻ መሆን፣
  2. ሚዲያው ለመንግሥት፣ ለበጎ አድራጎት ማኅበራት፣ ለዜጎች፣ ፍትሐዊ ተደራሽ መሆን፣
  3. ሚዲያው በአመራር ደረጃ ራሱን የቻለ መሆን፣ ናቸው፡፡

እስኪ እነዚህን ሦስት ነጥቦች ባጭሩ እንመርምራቸው፡፡

ፋይናንስ፡- በኢ.ቢ.ሲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 858/2006 አንቀጽ 14 መሠረት የኢቢሲ የበጀት ምንጮች ራሱ ከሚሰበስበው ገቢ፣ ከመንግሥት ድጋፍ እና ከሌሎች ምንጮች ነው፡፡ ስለዚህ ኢቢሲ ወጪውን ለመሸፈን ከአሰልቺ ማስታወቂያ ጋጋታ ገንዘብ ቢሰበስብ አይፈረድበትም፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚውም ሲመልሱ ልክ ናቸው፤ ለዚህም አይደል እንዴ ጨዋ ናቸው ያልኳችሁ፡፡ ከመንግሥት የሚደረገውን ድጋፍ በተመለከተ አዋጁ ምን ያክል ድጋፍ እንደሚያደርግ አልጠቀሰም፡፡ መቼም መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግለት መሥሪያ ቤት ለማን እንደሚያደላና ለማን እንደሚታዘዝ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡

በአመራር ራሱን የቻለ መሆን፡- 1ኛ. የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት በፓርላማው ይሾማሉ (አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ (2))፡፡ 2ኛ. ሥራ አስፈጻሚው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማው ይሾማል (አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ (1))፡፡ 3ኛ. ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች በዋና ሥራ አስፈጻሚው አቅራቢነት በቦርዱ ይሾማሉ (አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ (1))፡፡ ስለዚህ ሥራ አስፈጻሚው በኢቢሲ ላይ ያለው ረጅም እጅ ከዚህ ላይ ነው፡፡

ለመንግሥት፣ ለዜጎች፣ ለበጎ አድራጎት ማኅበራት ፍትሐዊ ተደራሽ መሆን፡- በአዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (4) የተለያየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ሚዛናዊ የሆነ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፍትሐዊ አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ይህን በተመለከተ አንባቢው ራሱ ይፍረድ፡፡

ዶ/ር አንዳርጋቸው ያነሷት አንድ ነጥብ አለች፡፡ “በመንግሥት ባለቤትነትና ቁጥጥር ሥር ያለ ሚዲያ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ‘(እና ሕዝብ)’ ጥቅም ለመስከበር ይሠራል፤ ይገደዳል” ይላሉ፡፡ ኢቢሲ ማለት እንደዚያ ነው፡፡

ታዲያ ፓርላማው ኢቢሲን ያቋቋመበትን አዋጅ እንደገና መፈተሽ ሲገባው ራሱ ባስቀመጠለት አቅጣጫ የሚጓዘውን ኢቢሲን መውቀጥ የራሱን ግመል የሚያክል ጉድፍ ተሸክሞ የሌላን ጉድፍ ላውጣልህ እንደማለት አይደለምን?

 

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s