መጽሐፈ አክሱም፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ሌላ መጽሐፍ እጃችን ገብቷል፡፡ ላውጋችሁ፡፡

መጽሐፈ አክሱም፡፡

መቼም ዘዋሪ ነኝና ሰሞኑን በጎግል መንደር ሳልፍ ከመጽሐፈ አክሱም ጋር ተያየን፡፡ መጀመሪያ በደንብ ስለማንተዋወቅ ልንተላለፍ ነበር፡፡ ግን “ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ” ነውና በደንብ ስንተያየ ተዋወቅን፤ በፍቅር ተቃቀፍን፡፡ እኔም ቸኮልኩና እያገላበጥኩ እየሳምኳት ወደ ቤቴ ይዣት ገባሁ፡፡ ጥቂት ወየብ ብላለች፤ ንግግሯ ሁሉ ግማሽ በግማሽ ፈረንሳይኛ ነው፤ ግማሹ ደ’ሞ በግዕዝ ነው፡፡ እኔ የፈረንሳይን ቋንቋ አልችልም:: ግን ያው ደህና (አስ)ተርጓሚ እስካገኝ ድረስ፣ ግዕዝ አልፎ አልፎ አንዳንድ ቃላትን ስለምሰማ በዚች ክፍተት ለመግባባት አፋችንና ዐይናችንን ፊት ለፊት ገጥመን ማውራት ጀመርን፡፡ የኔ ለንግግር ስለማይሆን ማዳመጡ ይሻላል ብዬ ጆሮዬን ሰጠኋት፡፡ ደግሞም “ነገር በዐይን ይገባል” ስለሚባል ዐይን ዐይኗን እያየሁ ጨዋታዋን ማዳመጥ ቀጠልኩ፡፡ ብዙ ነገር ብታጫውተኝም እኔ የተረዳሁት አንዳንድ ነገሮችን ብቻ ነው፡፡ የነገረችኝ ዋና ዋና ታሪኮች፣…

  1. ንግግሯን ከንግሥተ ሳባ ታሪክ መዝዛ ወደ አብርሃ ወአጽብሃ መጣች፡፡
  2. ስለ አክሱም ሐውልት፣ ስለ ርዝመታቸውና ስፋታቸው፣ ወድቆ ስለተሰበረው ትልቁ ሐውልት ስትተርክ ለጉድ ነው፡፡
  3. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስደቱ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከጠባቂዋ ከአረጋዊው ዮሴፍ እና ከአገልጋይዋ ከሰሎሜ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ የተረገጠውን የእግሩን ዱካ አስረግጣ ነግራኛለች፡፡ (ይህን ታሪክ ከአባቶቼ አንደበት ቀጥሎ በድርሳነ ዑራኤል ላይ ነበር ያነበብኩት፡፡)
  4. እነ ካሌብ፣ እነ ውድም፣ እነ ዘርአ ያዕቆብ፣ እነ በእደ ማርያም፣ እና ልብነ ድንግል፣ እነ ሠርፀ ድንግል ለአክሱም የሠሩትን ሥርዐት በሚገርም ለዛ ነግራኛለች፡፡

መሀል ላይ በ7316 ዓመተ ፍጥረት (በ1816 ዓ.ም) እንደተጻፈች ስትነግረኝ በመደነቅ እመለከታት ነበር፡፡

አብዛኛው ጨዋታዋ ግን ነገሥታተ-ኢትዮጵያ ለቤተ ክርስቲያን የጎለቱትን ጉልት በማውሳት ነበር፡፡ ከዚህ ላይ ጨዋታዋ ይበልጥ ሳበኝና ጆሮዬን ጣል አድርጌ በትኩረት ለማዳመጥ ተጋሁ፡፡

እንዲህ እያለች ወጓን ትቀጥላለች፣..

“በአኮቴተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ í አምላክ፡፡ ጎለትኩ አነ ንጉሥ እገሌገዳም/ቤ/ክ/ያን/…፡፡ እንዲህ ትጀምርና እነ አብርሃ ወአጽብሃ፣ ገብረ መስቀል፣ አንበሳ ውድም፣ ሰይፈ አርዓድ፣ (ቀዳማዊ) ዳዊት፣ ይስሐቅ፣ ዘርአ ያዕቆብ፣ በእደ ማርያም፣ ልብነ ድንግል፣ ገላውዴዎስ፣ ሚናስ፣ ሠርፀ ድንግል፣ ሱስንዮስ፣ ፋሲለደስ፣ (ቀዳማዊ) ኢያሱ፣ ሕዝቅያስ፣ (ቀዳማዊ) ተክለ ጊዮርጊስ፣ ጊጋር፣ (ሳልሳዊ) ዮሐንስ፣ የጎለቱትን ጉልት፣ ያበጁትን ሥርዐት ስትተርክልኛ የረታ አንደበቷ ይማርከኛል፡፡ እያንዳንዷን ጉልት ስትዘረዝራት ግሩም ያሰኛል፡፡

የዘመነ መሣፍንቶቹ ደጃዝማች ወልደ ሥላሴ፣ ሳባጋዲስ፣ ውቤ፣ ንቡረ ዕድ ኤርምያስ፣ የጎለቱትን ጉልት ስትተርከውም አፍ ታስይዛለች፡፡

መቼም መጽሐፈ አክሱም ጨዋታ አያልቅባት፤ በዚህ ልተገረም ነው? አለችና ቀጠለች፡፡ ተደላድለህ ቁጭ ብለህ ተቀመጥና የነገሥታቱን ታሪክ ልንገርህ፤ በደንብ አድምጠኝ አለችኝ፡፡ እኔም ጨዋታዋ ስለጣፈጠኝ፣ መከዳዬን ደገፍ አልኩና ጨዋታዋን መስማት ቀጠልኩ፡፡

ከዘርአ ያዕቆብ ጀምራ መጽሐፏ እስከተጻፈችበት ድረስ ያለውን የነገሥታቱን ታሪክና ዐበይት ክንውኖችን በሚገርም ቋንቋ ስትተርከው አጀብ ያሰኛል፡፡

በመሃል የዘመነ ሱስንዮስን ነገር ስትተርክ ዝናብ እንዳየ አድግ ጆሮዬ ይበልጥ ቆመ፤ ምክንያቱም በያዕቆባውያን (Jesuits) ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው መከራ ታቦተ ጽዮንም ከመንበሯ ተሰድዳ ነበርና ነው፡፡ እንደሚከተለው ነበር የተረከቺው፡፡

“…ወጸንዓ፡ መከራ፡ በስደት፡፡ ጽዮንሂ፡ ታቦተ፡ ሕግ፡ ተሰደት፡ በውእቱ፡ መዋዕል፡ ወበጽሐት፡ ውስተ፡ አሐቲ፡ ሀገር፡ እንተ መንገለ፡ ቡር፡ ዘትሰመይ፡ ድግሳ፡፡ ዕለተ፡ ስደታ፡ ወፀዓታ፡ እምአክሱም፡ ኮነ፡ በ7114 ዓመት፡ እምልደተ፡ ክርስቶስ፡ አመ፡ ሰዱሱ፡ ለወርኃ፡ ኅዳር፡ በዕለተ፡ ሰንበት፡ ቀዳሚት፡፡ ወተመጠውዋ፡ ደቅ፡ ድግና፡ በዓቢይ፡ ክብር፡ ወአንበርዋ፡ በጽኑዕ፡ ዑቃቤ፡ መጠነ፡ 12 ዓመት፡፡ ወሶበ፡ ተመይጠ፡ ሃይማኖት፡ እስክንድርያ፡ አተወት፡ ውስተ፡ ሀገራ፡ በዓቢይ፡ ክብር፡፡ አመ፡ 20 ወሰብዑ፡ ለሐምሌ፡ በዕለተ፡ እኁድ፡፡ በቀዳሚ፡ መንግሥቱ፡ ለንጉሥነ፡ ፋሲለደስ፡ ርቱዓ፡ ሃይማኖት፡፡…” ትርጓሜውም፤

“… (በሱስንዮስ) በዘመኑ መከራውና ስደቱ በጸና ጊዜ ታቦተ ጽዮን ተሰደደች፤ ድግሳ በምትባል ሀገር ቆየች፡፡ ከአክሱም ወጥታ የተሰደደችበት ዕለት በወርኃ ኅዳር በስድስተኛው ቀን ዓለም ከተፈጠረ በ7114ኛው ዓመት፣ ክርስቶስ በተወለደ በ1614ኛው ዓመት በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ነው፡፡ … በታላቅ ክብር ሰጡዋቸው፤ ለ12 ዓመታት ያክል በጥብቅ ጠባቂ አስቀመጧት፡፡ ሃይማኖቱ በቀና በንጉሣችን በፋሲለደስ የመጀመሪያ (የንግሥና) ዓመት የእስክንድርያ ሃማኖት በተመለሰች ጊዜ በሐምሌ 27 ቀን በዕለተ እኁድ በታላቅ ክብር (ወደ መንበረ ክብሯ) መለሷት/አስገቧት፡፡…” (ትርጉም የራሴ)

(ይህን ታሪክ ስትተርክልኝ እንግሊዙ ግራሃም ሐንኩክ ትዝ አለኝ፤ ይህ ሰው ታቦተ ጽዮንን እፈልጋለሁ ብሎ ሲኳትን ነበር፡፡ የሚገርመው ታቦተ ጽዮን በዘመነ ሱስንዮስ መሰደዷንና አላወቀም፡፡ (ወደ አማርኛ “ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ” ተብሎ የተተረጎመውን የፈላጊውን መጽሐፍ ገጽ 102 ላይ ያለውን ይመልከቱት፤ እንግሊዙ ይህን ታሪክ እንዳላወቀው ያረጋግጣል፡፡ እርሱ የሚያውቀው በግራኝ ጦርነት ምክንያት እንደተሰደደችና በፋሲለደስ ዘመን ወደ መንበሯ እንደተመለሰች ነው፡፡)

ወደ መጨረሻው አካባቢ የነገረችኝ ነገር ደግሞ ማን እንደጻፋት ለማወቅ ብዙ እንዳልደክም “… ናሁ፡ ጸሐፍነ፡ ካህናተ፡ ጽዮን፡ ታሪከ፡ ሥልጣኑ፡ ወኃይሉ፡…” በማለት አሳርፋኛለች፡፡ ጨዋታችንም በዚሁ አበቃ፡፡ ሌላ ጊዜ በደህና አስተርጓሚ እንደምታወጋኝ ወይም እኔ ቋንቋዋን አጥንቼ ስመጣ በሙሉ መንፈስ እንደምንግባባ ቃል ገብተን ተለያየን፡፡

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s