ብድር – ሉአላዊነት – ልማት

በቀ/ኃ/ሥ ዘመን በአንድ ወቅት የኢጣሊያ መንግሥት 35 ሚሊዮን ብር ብድር ይሰጣል፡፡ ብድሩ መጽደቅ ስለነበረበት በሕግ መምሪያ ም/ቤት በኩል ያለምንም ችግር ጸደቀ፡፡ ቀጥሎ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀረበ፡፡ (የሕግ መወሰኛ ም/ቤቱ የላይኛው የም/ቤት መዋቅር ነበር፡፡)

የሕግ መወሰኛ ም/ቤቱ ሰባት አባላት ያሉት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጉዳዩን አጣርቶ እንዲያቀርብ ያዛል፡፡ በዚህ መሠረት የብድር ውሉ ሲመለከቱት አንቀጽ 10 ስለ ብድሩ አከፋፈል እንዲህ ይላል፤

“በዚህ የብድር ውል አከፋፈል ላይ ክርክር ቢነሳ ዳኝነቱ ሮም ላይ ሆኖ በኢጣሊያ ሕግ መሠረት ይታያል፡፡” ይላል፡፡

የኮሚቴው አባል የነበሩት አቶ አመዴ ለማ (በኋላ ፊታውራሪ) ይህን የውሉን አንቀጽ ሲመለከቱ “ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ተንኮልና ደባ የፈጸመች አገር ስለሆነች አሁንም ተመሳሳይ በደልና ተንኮል ለመፈጸም አቅዳለች፡፡” በማለት የብድር ውሉን አልቀበልም አሉ፡፡

(ታሪክ፡- በአጼ ምኒልክ ጊዜ ኢጣሊያ 2 ሚሊዮን ሊሬ አበድራ ነበር፡፡ ይህን ብድር በማስታከክ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመዳፈር ስታደባ ወዲያውኑ የነቁት አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ “የጭራ ብር” አዋጣ ብለው በያንዳንዱ ሰው ቤት ውስጥ ባለው የጋማና የቀንድ ከብት ብዛት ልክ እንዲያዋጣ አድርገው ብድሩ ተከፈለ፡፡ የኢጣሊያ ተንኮል ተኮላሸባት፡፡ እግረ መንገዱን “የጭራ ብር” የተዋጣበት ዘመን የጊዜ መቁጠሪያ ሆኗል፡፡)

የአቶ አመዴን ሀሳብ ከሰባቱ የኮሚቴው አባላት ስድስቱ ተቀበሉት፡፡

በኋላ ላይ የሕግ መወሰኛው ም/ቤት የብድር ውሉን አልቀበልም አለ፡፡ ጉዳዩ ጃን ሆይ ጋር ደረሰ፡፡

ጃን ሆይ፡- “እንዴት ለሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ብድር አንቀበልም ትላላችሁ? ከኢጣሊያ ጋር ድሮ ተጣልተን ነበር፤ አሁን ሰላም ወርዶ ጥሩ ግንኙነት እያለን እንዴት ብድር አንቀበልም ትላላችሁ?” ብለው በቁጣ ተናገሩ፡፡ ከዚያም ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ የሚል ደብዳቤ ለም/ቤቱ ይጻፋል፡፡

ይህን የጃን ሆይ ‘ደብዳቤ’ የም/ቤቱ ዐቃቤ ጉባኤ የነበሩት ጄ/ል ዐብይ አበበ ለም/ቤቱ አነበቡ፡፡ የም/ቤቱ አባላት ደነገጡ፡፡ ከዚያ በኋላ ክርክሩ ቀጠለ፡፡

አቶ አመዴ፡- “እኔ በበኩሌ ንጉሠ ነገሥቱ ይህን ደብዳቤ መጻፋቸው ትክክል ናቸው፡፡”

ም/ቤቱ፡- “ምክንያቱስ?”

አቶ አመዴ፡- “ለግርማዊ ጃንሆይ የተነገራቸው “የጠላት ገንዘብ አንበደርም” በሚል መልኩ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ከሆነ የተነገራቸው ትክክል ናቸው፡፡”

ቀጠል አደረጉና “በሌላ መልኩ ደግሞ ግርማዊ ጃን ሆይ ይህን ደብዳቤ ለፓርላማ ጻፉ ብዬ አላምንም፡፡”

ም/ቤቱ፡- “ምክንያቱስ?”

አቶ አመዴ፡- “ምክንያቱም ንጉሠ ነገሥቱ ፓርላማውን አስገድደው ያስወስኑ ነበር የሚል በማስረጃ የተደገፈ ሬኮርድ ያለው ደብዳቤ አይጽፉም፡፡” ይህን ጊዜ የንግግሩ ቅኔ የገባቸው የም/ቤቱ አባላት አጨበጨቡ፡፡ በም/ቤቱ ውስጥ በርካታ የሀገር ፍቅር ያላቸው ተወካዮች አሉ፡፡ (የአቶ አመዴ ንግግር ደብዳቤውን የጻፉት ጃን ሆይ ሳይሆኑ ሚኒስትሮቹ ናቸው ለማለት ነው፡፡)

የም/ቤቱ አባላት፡- “እንዴት ይህን የሀገር ክብር የሚነካ ነገር እንቀበላለን?” በማለት ተቃወሙ፡፡

ደጃዝማች ፀጋዬ (የኮረም ተወካይ)፡- “ልጅ ይልማ ደሬሳ፤ ሂድና አጼ ኃ/ሥላሴን “እርስዎ እኮ የግል መሬት የለዎትም፤ መሬት የሕዝብ ነች፤ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ አያገባዎትም” ብለህ ንገራቸው፡፡” አሉ፡፡

ደጃዝማች ወርቅነህ (የጎጃም ተወካይ)፡- “ስማ ልጅ ይልማ ደሬሳ ኢጣሊያ እኮ አስር ሳንቲም አላበደረንም፡፡ ላበድራችሁ የሚለው የኛ ሚኒስትሮች እየወሰዱ ኢጣሊያ ባንክ ያስቀመጡትን የራሳችንን ገንዘብ ነው፡፡ እናንተ ግን እዚህ ም/ቤት ያሉ አያስቡም ብላችሁ ከሆነ ልክ አይደላችሁም፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅምና ጉዳት ለይተን የምናውቅ ነን፡፡ ሂድና ለጃን ሆይ “ብድሩን ሰርዘናል” ብለህ ንገራቸው፡፡” አሉ፡፡

ከዚያም ብድሩ ተሰረዘ፡፡

ማምሻውን አቶ አመዴ ለማን ሲያስፈራሩት አደሩ፡፡

በማግሥቱ  ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ የሚል ሀሳብ ቀርቦ ጉዳዩ እንደገና ለክርክር ቀረበ፡፡

(እዚህ ላይ ዐቃቢ ጉባኤው ጄ/ል ዐብይ አበበ ቦታቸውን ለምክትሉ ሰጥተው ወርደው ተቀመጡና ከሌሎች ጋር ሆነው የብድሩን መሰረዝ ሲደግፉ ዋሉ፡፡)

አሁንም ብድሩ እንዲሰረዝ ተወሰነ፡፡ ጉዳዩ እየከረረ መጣ፡፡

ጃን ሆይ የተወሰነ ሰው መጥቶ ያስረዳኝ አሉ፡፡ በዕድሜ ሽማግሌ የሆኑ የም/ቤት አባላት ብቻ ተመርጠው ሄዱ፡፡

ጃን ሆይ፡- “እስቲ ጉዳዩን አስረዱኝ፡፡” አሉ ተመርጠው የሄዱትን አባላት፡፡

ተመርጠው የሄዱት አባላት፡- “ግርማዊ ሆይ የስምንት ቀናት ክርክር እንዴት እናስረዳዎት? ቃለ ጉባኤው ስላለ ለምን ቃለ ጉባኤው አይነበብም፡፡” አሉ፡፡

ቃለ ጉባኤው ቀርቦ እንዲነበብ ጄ/ል ዐብይ አበበ ይታዘዛሉ፡፡ ጄ/ል ዐብይ አበበ አቶ ክፍሌ እንግዳ ቃለ ጉባኤውን ይዘው እንዲያነብቡ አደረጉ፡፡ ለ6 ሰዐታት ያክል ቃለ ጉባኤው ጃን ሆይ ፊት ተነበበ፡፡

ጃን ሆይ፡- “በአንቀጽ 10 ላይ አከፋፈልን በተመለከተ የሠፈረው ትክክል ስላልሆነ እንዲሰረዝ፡፡” ብለው ወሰኑ፡፡

ይህ በሆነ በ3ኛው ዓመት አንቀጽ 10 ይስተካከልና ብድሩ ተመልሶ ይመጣል፡፡ ብድሩ በፓርላማ ይደገፍና አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ያንን 35 ሚሊዮን ብር ይረከብና የለገዳዲ ግድብ እንዲሠራበት ተደረገ፡፡

 

ምንጭ፡- ፊታውራሬ አመዴ፣ የሕይወት ታሪኬ፣ 2003 ዓ.ም

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s