የሕግ ት/ቤቶችና ቋንቋ በኢትዮጵያ–ካልአይ ክፍል (የመጨረሻ)

ሕግ ትምህርትና አማርኛ

በአሁኑ ወቅት የሕግ ትምህርት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ከ/ት/ተ) እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ ከ1994 ዓ.ም ወዲህ የሕግ ትምህርት ቤቶች በመንግሥትም ሆነ በግል ከ/ት/ተ ዘንድ በመደበኛ፣ በማታ፣ በተከታታይና በርቀት መርኀ-ግብር እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የሕግ ት/ቤቶች ቁጥራቸውም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል፡፡ የቁጥሩ ማደግ የራሱ የሆነ በጎ እና አሉታዊ ጎኖች ቢኖሩትም ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን የሕግ ትምህርት በመንግሥት ከ/ት/ተ ብቻ እንዲሰጥ ተወስኗል፤ በርቀት መርኀ-ግብር እንዳይሰጥም ተከልክሏል፡፡ (ነገር ግን አንዳንድ የግል ከ/ት/ተ ዛሬም ድረስ በስርቆት የሕግ ትምህርት እየሰጡ እንዳሉ ይታወቃል-“ግመል ሰርቆ አጎንብሶ” የሚለውን አባባል ልብ ይሏል፡፡)

ታዲያ የተማሪዎች፣ መምህራንና የሕግ ትምህርት ጉዳይ ካነሳነው የቋንቋ ጉዳይ እንዴት ነው ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ በከ/ት/ተ ላይ በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ናቸው፤ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአንድ የከ/ት/ተ ውስጥ ሕግ የሚያስተምሩ መምህራን እንደዚሁ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ናቸው፡፡ እንደ ቀድሞው አይሁን እንጅ የውጭ ሀገር መምህራን (በአሁኑ ዘመን በተለይ ሕንዳውያን) በሕግ ት/ቤቶች ውስጥ ያስተምራሉ፡፡ እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የሕግ ትምህርት ከተጀመረ ወዲህ የማይለዋወጠው ነገር የማስተማሪያ ቋንቋው ነው፡፡ ይኸውም እንደቀድሞው ሁሉ እንግሊዝኛ መሆኑ ነው፡፡ የትምህርቶቹ ዓይነቶች ከበፊቱ በመጠኑ ሰፋ ቢልም ዋና ዋናዎቹ መሠረታዊያንና የሥነ-ሥርዐት ሕጎች ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ ገዥው ሕግ ደግሞ አማርኛ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ የማስተማሪያ ቋንቋው እንግሊዝኛ ቢሆንም አማርኛውን የሕጉን ክፍል ማወቅ ግን የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁንም በድጋሚ ገዥው ቅጅ እርሱ ነውና፡፡ የህጎቹን ነገር ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ውጭ በተለይ በአንዳንድ ክልሎች በሥራ ቋንቋቸው እየወጡ እንደሆነ ከፍ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ቋንቋን በተመለከተ በተለይ በአሁኑ ወቅት ጉልህ ችግር እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህንም ከዚህ በታች ለመዘርዘር እሞክራለሁ፡፡

ተማሪዎች ዘንድ ያለ የቋንቋ ችግር

የቋንቋ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑና ያልሆኑ ብለን ለሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ በመሠረቱ የሕግ የቋንቋ ችግር በሁሉም ተማሪዎች ዘንድ የሚስተዋል ቢሆንም በተለይ አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባልሆኑ ተማሪዎች ላይ ይበረታል፡፡

ሀ. አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆነ ተማሪዎች፡ እነዚህ ተማሪዎች ዋና ችግራቸው የአማርኛ ቋንቋ እጥረት ሳይሆን ሕጉ የሚጠቀምባቸውን የአማርኛ ቃላት አለማወቃቸው ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ውስጥ የሚማሩት በእንግሊዝኛ ስለሆነ አቻ አማርኛ ትርጉሙን ምንም ትኩረት ሳያደርጉበት እንዲሁ የትምህርት ዓመቱ ይገባደዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ለምሳሌ በእንግሊዝኛ “Period of limitation” በአማርኛ “ይርጋ” እንደሚባል ሳያውቁት ሊመረቁ ይችላሉ፡፡ ይህን እንደ ምሳሌ ጠቀስኩት እንጅ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የሕግጋቱን አማርኛ ቅጅ ስለማያነቡት የአማርኛ ትርጉሙን ለማወቅ ሲቸገሩ በስፋት ይታያል፤ ያወቁት ጊዜ ደግሞ መገረም ይስተዋልባቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን፣ መጥሪዎችን፣ አቤቱታዎችን፣ የፖሊስ የምርመራ ሰነዶችን፣ የዐቃቤ ሕግ መዝገቦችንና የመፋረጃ ሃሳቦችን፣ መጻሕፍትን፣ ሌሎች ሕግ ነክ ጽሑፎችን የማግኘትና የማንበብ ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ከአማርኛ ጋር ያለው ክፍተት እንደተንገረበበ ይቆያል፡፡ አንዳንዴ በአስተማሪ እርዳታ ወይም ግፊት ወይም አቅርቦት የመመልከት ዕድል ይኖራቸዋል፤ እንደሚታወቀው ይህ ደግሞ በአስተማሪው ትጋት ይወሰናል፡፡

ይህ የቋንቋ ክፍተት ከተመረቁ በኋላ ይከተላቸውና በሥራ ዓለም ውስጥ መቸገር፣ እስኪለምዱት ድረስ ብዙ መታሸት ይኖራል፡፡ ይህም በሕግ ዕድገትና በፍትሕ አሰጣጥ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል፡፡

ለ. አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆነ ተማሪዎች፡ በርግጥ እነዚህ የተማሪ ክፍሎች ሁሉንም አያካትትም፤ ቢሆንም የአንድ ተማሪ ጉዳይ ቢሆንም እንኳ ሊያሳስበን ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ነው አማርኛን የተሻለ የሚያውቁትና ለቋንቋውም ቅርበት የሚኖራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ ከፍተኛ መሻሻል ሲያሳዩ አንዳንዶች ደግሞ ይህ ነው የማይባል ለውጥ ሳያመጡ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡

እነዚህ ከላይኞቹ አንጻር ሲታይ የሕግጋቱን የአማርኛ ቅጅ ቢያገኙ እንኳ ፈጽሞ ማንበብ የማይችሉ፣ በከፊል ማንበብ የማይችሉና፣ በደንብ ማንበብ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በከፊል ማንበብ የሚያዳግታቸው በሂደት ከአማርኛው ተዋውቀው ለመረዳት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከላይኞቹ ምድቦች ላይ ያነሳነው ችግር እኩል ከዚህ ጋር ስለሚንጸባረቅ ከአቻ የአማርኛ የሕግ ቃላት ጋር ያላቸው ርቀት ሳይጠብ ይዘልቃል፡፡

እንዲሁም አማርኛን ፈጽሞ የማይችሉ ተማሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ለአማርኛ የሕግ ቃላት በጣም ርቀው እናገኛቸዋለን፡፡ ከላይ የጠቀስነውን ችግር ከዚህ ላይ ስንደምረው የችግሩ ሥር እየጠነከረና እየራቀን ይሄዳል፡፡ በነዚህ ተማሪዎች ዘንድ አማርኛ ሕግጋትን ማንበብ፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን፣ ማብራሪያዎችን ማንበብና መረዳት የማይታሰብ ይሆናል፡፡

በመምህራን ዘንድ ያለ ችግር

የሕግ መምህራን ያለባቸው የቋንቋ ችግር ከተማሪዎቹ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ምናልባት የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ሊያንስ ይችላል፡፡ መምህራኑ የተማሩት ያው በእንግሊዝኛ ስለሆነ፣ አፍ መፍቻ ቋንቋቸውም ከአማርኛ ሌላ ሊሆን ስለሚችል ከላይ የተማሪዎችን ችግር የተብራራው መምህራኑም ላይ ይስተዋላል፡፡

በርግጥ መምህራኑ በተለያየ የሥራ አጋጣሚ ለምሳሌ በዳኝነት፣ በዐቃቤ ሕግነት፣ በጥብቅና፣ እንዲሁም በሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግለው ከሆነ ችግሩን ያስወግዱታል፡፡ በቋንቋ ረገድም በነዚህ የሥራ ዘርፎች ላይ ሠርተው የነበሩ መምህራን በማስተማር ዘንድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ፤ ተመራጭም ናቸው፡፡ እንዲሁም ከሥራ ልምድ፣ ሕግ-ነክ ሆነ ከዚያ ውጭ ያሉ ጉዳዮችን ከማንበብ የተነሳ የአማርኛ የሕግ ቋንቋ ችሎታቸው ከፍ የማለት ዕድሉ አለ፡፡ ይህን እሴት ለተማሪዎቹ ማጋራት ደግሞ ከመምህራኑ የሚጠበቅ ትልቅ ድርሻ ነው፡፡

ነገር ግን በአዳዲስ የሕግ መምህራንና ከምረቃ በኋላ ቀጥታ የሕግ መምህር የሚሆኑ ሰዎች አማርኛ የሕግ ቋንቋ ችሎታቸው ከተማሪዎቹ ያን ያክል ተሽሎ አይታይም፡፡ ምክንያቱም አማርኛውን የሚያውቁበት ዕድል የላቸውምና፡፡ የሕግጋቱን አማርኛ ቅጅ፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን፣ ማመልከቻዎችን፣ ማብራሪያዎችን፣ የማያነቡ መምህራን ለአማርኛው ያላቸው ርቀት ልክ እንደተማሪዎቹ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎችም በእነርሱ ዕውቀት ልክ ተሰፍተው ይወጣሉ፡፡

በመማር-ማስተማሩ ሂደት ላይ የሚፈጥረው ችግር

በተማሪዎችና በመምህራን ላይ ያለው የአማርኛ ቋንቋ ችግር በመማር-ማስተማሩ ሂደት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡ በተለይ በተማሪዎች ዘንድ ያለው ችግር በመማር-ማስተማሩ ሂደት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ፈታኝ ሆኖ ይታያል፡፡ ለአስተማሪው የሚያስተምረውን ትምህርት በተግባር ለመደገፍ፣ ተማሪዎችን እውነተኛ የሕግ ጉዳዮችን እንዲከታተሉ ለማስቻል ያዳግታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የከ/ት/ተ የሕግ መምህር የሚያጋጥመው ችግር በተለይ አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆነ ተማሪዎችን ከሌሎች ጋር እኩል ለማስኬድ አለመቻል ነው፡፡ ይኸውም እነዚህ ተማሪዎች በአማርኛ የተጻፉ መጻሕፍትን፣ ማብራሪያዎችን፣ ሕግጋትን፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን እንዲሁም በፈተና ወቅት ማንበብና መረዳት ስለማይችሉ ይህን ክፍተት ለመሙላት ሌላ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡

የሕግ ትችት፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን ዳሰሳና ትችት፣ የቤት ሥራዎችን እንዲሠሩ ቢያደርግ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተማሪዎቹንም መምህሩንም ሲጎዳ ይታያል፡፡ አማርኛ አንችልም ይህን አንሠራም፣ አናነብም የማለት አዝማሚያ፣ ፈተናው እውነተኛ ጉዳይ የተመለከተ እንደሆነ በቋንቋ ሰበብ ማድረግ፣ … በጣም ሲበረታ ደግሞ ፈጽሞ አማርኛ ገዥ ቅጅ ስለመሆኑ አለመረዳት አለ፡፡ መምህር መቼም ይህን ሁሉ ችግር የመቅረፍ ጊዜውም፣ አቅሙም፣ ገንዘቡም አይኖረውም፡፡ ይህም ሆኖ መምህራን የተቻላቸውን ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በይበልጥ ግን ሁሉንም ተማሪዎች የሕግጋቱን አማርኛውን ቅጅ ችላ እንዳይሉ ይልቁንም ከእንግሊዝኛው ጋር እኩል ትኩረት እንዲያደርጉበት ከማስተማር ችላ ያሉበት ጊዜ አይኖርም፡፡ የፖለቲካ ጥያቄውን ወደ ጎን አድርገው የሕግ ጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ከማሳሰብ ቦዝነው አያውቁም፡፡

ተማሪዎች አማርኛውን ችላ ቢሉትና ትኩረት ቢነፍጉት፣ ቋንቋውን አለማወቅ ጥፋት ሆኖ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ተመርቀው ከወጡ በኋላ በሥራ ዓለም ላይ ከዕለት ዕለት የሚያጋጥማቸው ጉዳይ መሆኑ ላይ ነው፡፡

የችግሮቹ ውጤት ምን ሊሆን ይችላል?

ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ማጠንጠኛቸው አንደኛ የሕግጋቱ ገዥ ቅጅ አማርኛው መሆኑ፣ ሁለተኛ (በዚሁ ምክንያት) አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥትና የሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም የአራቱ ክልሎች የሥራ ቋንቋ ስለሆነ የሕግ ምሩቃን ወደነዚህ ቦታዎች ሄደው ለመሥራት ከፍተኛ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ሦስተኛም ሀገር አቀፍ ተፈጻሚነት ያላቸው ሕግጋት በሁሉም ክልል ተፈጻሚነት ስላላቸውና ገዥው ቅጅ ደግሞ አማርኛ በመሆኑ ነው፡፡ በመቀጠልም በአዋጅ ቁጥር 454/97 መሠረት የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በሁሉም ፍ/ቤቶች (የክልል ፍ/ቤቶችን ጨምሮ) አስገዳጅ ነው፡፡ ይህም ማለት እንደ ሕግ ነው የሚቆጠሩት ለማለት ነው፡፡ የፌዴራል ሰበር ውሳኔዎች የሚሰጡት ደግሞ በአማርኛ ብቻ ነው፤ እስካሁን ድረስ ወደ ሌላ ቋንቋ የመተርጎም ዕድል አላገኙም (ጥቂቶቹ ይፋዊ ባይሆነም ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉመዋል፡፡) እንዲተረጎሙ የሚያስገድድ ሕግም የለም፡፡ አንድ ላይ ቢታተሙም እንደ ሌሎቹ ሕግጋት የትርጉም መሥፈርት የለባቸውም፡፡

የሰበር ውሳኔዎችን በተመለከተ በተግባር እንደሚታየው ሁሉ ዳኛ፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ጠበቃ፣ የሕግ መምህር ሆኖ የሚሠራ ነገር ግን የሰበር ውሳኔዎች የማይጠቀም ከሆነ ሰነፍና ብቃት የሌለው እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ እነዚህን የማያውቅ ዳኛ ከሆነ ፍርድ ያዛባል፤ ጠበቃ ከሆነ እነዚህን የሚያውቅ ተከራካሪ ጠበቃ ከገጠመው ክፉኛ ተረትቶ ደንበኛውን ይበድላል፤ ዐቃቤ ሕግ ከሆነም የመንግሥትን ጥቅም ይጎዳል፤ መምህር ከሆነ ደግሞ ተማሪዎቹን በድሎ ሕዝብንም ሊበድል ነው ማለት ነው፡፡ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ይህን ያህል ርቆ ወይም ጠልቆ ሊሄድ ይችላል፡፡

የመፍትሔ ሀሳቦች

ሕግ ትምሀርት ቤቶች የፍትሕ ሥርዓቱ የማይነጥፉ፣ የማይደርቁ መጋቢ ምንጮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ምንጭነታቸው ብቁ የሰው ሃይል እንዲያፈሩ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጥልባቸዋል፡፡ ታዲያ ከላይ የተብራራውን የሕግና ቋንቋ ችግር እንደምን ይፈታል፣ መፍትሔዎቹ ምን ይሆኑ የሚለውን ምልከታዬን ላስቀምጥ፡፡ ለጊዜው እኔ አንዱን መፍትሔ የመሰለኝን ነገር በአጭሩ ከዚህ በታች አብራራለሁ፡፡

አማርኛን በከ/ት/ተ ሕግ ት/ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ ማድረግ፡ አማርኛ የህግጋቱ ገዥ ቅጅ እንደሆነና በሥራ ላይ የሚውለውም አማርኛው እንደሆነ አበክሬ ተናገሬያለሁ፡፡ በተለይ ከፈረንሳይኛ አንጻር ስንመለከተው የአማርኛ እንደ አንድ ትምህርት መሰጠት ትልቅ ሚዛን አለው፡፡ ፈረንሳይኛ የባሕረ ሕግጋቱ አያት ቋንቋ ስለሆነ ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ አማርኛ ግን ተፈጻሚው፣ አስገዳጅ፣ ገዥ፣ ሥራ ላይ ያለው ቋንቋ በመሆኑ አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ የለውም፡፡

በምን ዓይነት መልኩ ይሰጥ የሚለውን በተመለከተ እንደ ፈረንሳይኛ ሁሉ በአማራጭ ትምህርት ቢሰጥ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በቅድሚያ አማርኛ ግዴታ የሚሆን ከሆነ የሕግ ትምህርት ሕግ መሆኑ ይቀርና የቋንቋ ት/ቤት ሆኖ እርፍ እንዳይል ይጠብቀዋል፡፡ በመቀጠልም (በግንዛቤ እጥረት የተነሳ) መማር አንሻም የሚሉ ተማሪዎች ቢኖሩ ግዴታ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡

ትምህርቱም ቢያንስ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ወሰነ ትምህርቶች ተሰጥቶ ቢታይ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ይህም ተማሪዎች ከሕግ ቃላት ጋር እንዲተዋወቁ በር ስለሚከፍት፣ ተማሪዎች ለአማርኛ ቅጅው ትኩረት እንዲሰጡ ስለሚያነሳሳቸው፣ አማርኛ በጣም ለሚቸግራቸው ተማሪዎችም ቀሪውን የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡

አስተማሪዎቹ ደግሞ አማርኛ ቋንቋ ምሩቃን ሆነው ቢያንስ የሕግ ዲፕሎማ ቢኖራቸው ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም አማርኛው ለሕግ ተማሪዎች ስለሚሰጥ ከሕግ ትምህርቱ የራቀ ጉዳይ/ትምህርት ላይ እንዳያተኩሩ ነው፡፡

ሌሎች እናንተ የምታስቧቸው መፍትሔዎች ካሉ/ለ እባክዎ ከምክንያት ጋር ያቅርቡ፡፡

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s