የሕግ ት/ቤቶችና ቋንቋ በኢትዮጵያ _ ቀዳማይ ክፍል

የሕግ ት/ቤቶችና ቋንቋ በኢትዮጵያ

  1. ጠቅላላ መግቢያ

ዘመናዊ የሕግ ት/ቤት በኢትዮጵያ የተጀመረው በ1955 ዓ.ም በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የያኔው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤትን ሲከፍት በሀገሪቱ ያለውን የህግ ምሁራን እጥረት ለመቅረፍ እንደነበር የሚታወስ ነው፤ ምክንያቱም በወቅቱ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የሕግ ምሁራን ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል ሳይሆን እጅግ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነበር፡፡ የሕግ ት/ቤቱ ሲጀመር አብዛኛዎቹ መምህራን ከውጭ አገር የመጡ በተለይም ከአሜሪካና ከአውሮፓ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለን የሕግ ሰዎች በአካለ ባናውቃቸውም እንኳ በጻፏቸው ዘመን ተሻጋሪ መጻሕፍት፣ መጣጥፎች፣ … በቅርብ የምናውቃቸው ያህል ይሰማናል፡፡ (በርግጥ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እነርሱን መዘከር አይደለም፡፡)

የቀ/ኃ/ሥ ሕግ ት/ቤት ከመቋቋሙ በፊት ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ባሕረ ሕግጋት ማለትም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ (1949)፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ (1952)፣ የባሕር ሕግ (1952)፣ የንግድ ሕግ (1952)፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዐት ሕግ (1954) ታውጀው ነበር፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዐት ሕግ ደግሞ ሕግ ት/ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ ሦስት ዓመት ዘግይቶ በ1958 ዓ.ም ነው የታወጀው፡፡ የዘመኑ ሕገ-መንግሥትም በ1948 ዓ.ም ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ እንግዲህ እነዚህን ዐበይት ሕግጋት የሚያስፈጽና የሚተረጉም የሰው ሃይል ለመግኘት ይመስላል ሕግ ት/ቤቱ እንዲቆም/እንዲመሠረት የተደረገው፡፡ እነዚህን ሕግጋት የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው ከአውሮፓና ከአሜሪካ ተቀጥረዋል፡፡ ከዚህ ላይ አንባቢው የታወጁት ሕግጋትና የመምህራኑ ነገር እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን እርስ በእርስ ተያያዥነት ያላቸው ክንውኖች እንደሆኑ ሊያስተውል ይገባል፡፡ ታዲያ ማን ያረቀቀውን ሕግ ማን ያስተምረዋል?

የሕግ አርቃቂዎቹ ደግሞ እነ ፕ/ር ሬኔ ዳዊት፣ ፕ/ር ኢስካራ፣ ፕ/ር ዣን ግራቨን፣ ሰር ቻርለስ ማቴዎስ እና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡ ከሁለቱ የሥነ-ሥርዓት ሕጎች ውጭ ሌሎቹ መሠረታዊያን ሕግጋት ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ ከዚያም ወደ አማርኛ ነበር እየተተረጎሙ የቀረቡት፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ የተዘረዘሩቱ የሕግ ምሁራን ባረቀቋቸው ሕግጋት ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማብራሪያዎችን፣ ትንታኔዎችን፣ አዘጋጅተው እስካሁን ድረስ ተማሪውም፣ መምህሩም፣ ጠበቃውም፣ ፍ/ቤቱም፣ ዐቃቤ ሕጉም…እየተገለገልንባቸው እንገኛለን፡፡ መቼም የጽሑፋቸው ነገር ለቅል ነው፡፡ ታዲያ ዝም ብሎ የሙጢኝ የሚል አለ መሰላችሁ?

እነዚሁ ምሁራንና በቀ/ኃ/ሥ ሕግ ት/ቤት ያስተምሩ የነበሩ ሌሎች ምሁራን የሚያስተምሩበት የነበረው ቋንቋ እንግሊዝኛ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት እንዲሁ ሳይሆን የራሱ የሆነ ምክንያት እንዳለው እገነዘባለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አስተማሪዎቹ የውጭ አገር ሰዎች በመሆናቸው ወይም ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገር ስለመጡ ነው፡፡ ታዲያ ከፈረንሳይ፣ ከስዊዝ፣ ከቼኮዝሎቫኪያ … አገር የመጡ መምህራን እንዳሉ እናስተውል፡፡ ቢሆንም ግን ከነዚህ ሃገራት የመጡ መምህራንም ቢሆን በዓለም አቀፉ ቋንቋ ነበር ሲያስተምሩ የነበሩት፤ የጻፉትም እንዲሁ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሕግጋቱ የሚገኙት በእንግሊዝኛና በአማርኛ መሆኑ ነው፡፡ በላዩ ላይ ደግሞ እንግሊዝኛ የዐለም ቋንቋ በመሆኑና የዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ ቋንቋ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለሕግ ተማሪዎች ይሰጥ ነበር፤ አሁንም ድረስ እንደ አንድ የትምህርት ዐይነት ለሕግ ተማሪዎች ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጅ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ ፈረንሳይኛ ቋንቋ በአማራጭነት ይሰጣል፤ አሁንም ድረስ፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተጠቀሰው በተለይ የመሠረታዊያን ባህረ ሕግጋት የመጀመሪያው ቅጅ ፈረንሳይኛ በመሆኑ ነው፡፡ በሕግ አተረጓጎም ዘንድ አንዳንድ ጊዜ የፈረንሳይኛውን ቅጅ እስከማመሳከር የሚያደርስ ጉዳይ ስለሚያጋጥም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ነው ፈረንሳይኛ በአማራጭነት እንዲሰጥ የተደረገው፡፡

  1. ሕግና የተፈጻሚነት ወሰኑ

የሕግ ተፈጻሚነት ያ የወጣው ሕግ የሚመለከታቸው ማንኛውንም/ሁሉም ሰዎች (የተፈጥሮም ሆነ በሕግ ሰውነት የተሰጣቸው) እንዲገዙበት ነው፡፡ አንዳንድ ሕጎች ደግሞ ሁሉም ሰው እንዲገዛባቸውና እንዲያከብራቸው የሚጠይቁ ስለሆነ በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ዜጎች ሊከተሉትና ሊያከብሩት የሚገባ ነው፡፡ አስገዳጅነቱም በሁሉም ሰዎችና አካላት ዘንድ ይሆናል፤ ይህም በመላ ሀገሪቱ ያሉ ዜጎች፣ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት የሚገዙበት ነው፡፡

እንግዲህ ሕግ የምንለው በሕግ አውጭው አካል ጸድቆ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የወጣውን እንደሆነ የነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 3/1987 ዓ.ም አንቀጽ 2 ይደነግጋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ሁለት የማይታለፉ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቆም ላድርግ፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕግ አውጭ ምክር ቤቱ ለሚያወጣቸው አዋጆች እንዲሁም የሚኒስቴሮች ም/ቤት ለሚያወጣቸው ደንቦች ማስፈጸሚያ የሚሆኑ መመሪያዎች፣ የሕግ ክፍል ማስታወቂያዎች፣…በነጋሪት ጋዜጣ የመታተም ዕድል የላቸውም፡፡ ነገር ግን “በነጋሪት ጋዜጣ ስላልታተሙ ተፈጻሚነት የላቸውም” ለማለት የማይቻል ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡[1] በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውና ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ወደ አማርኛ ተተርጉመው በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው መውጣት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ሥነ-ሥርዐት አለመጠበቁ እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከተፈጻሚነት የሚያግዳቸው እንደሌለ ልንረዳ ይገባል፡፡

ሕግጋቱ የሚታተሙበት ቋንቋ አማርኛና እንግሊዝኛ እንደሆነ ከላይ የተጠቀሰው አዋጅ ያስቀመጠ ሲሆን በሁለቱ ቅጅዎች መካከል አለመጣጣም ሲኖር ገዥ የሚሆነው የአማርኛው ቅጅ እንደሚሆን አብሮ ተቀምጧል፡፡ እንግዲህ ይህ ሕግ የሚመለከተው ከ1987 ዓ.ም በኋላ የሚወጡትን ሕጎች ነው፡፡ ታዲያ ከ1987 ዓ.ም በፊት የወጡትና አሁን ድረስ ሥራ ላይ ያሉት ሕጎች እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከ1987 ዓ.ም የወጡት ሕጎች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ሲሆን ገዥው ቅጅ አማርኛ እንደሆነ ቀድሞ ይሰራበት የነበረው የነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1/1934 ይደነግጋል፡፡ (ይህ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 3/1987 ተተክቷል፡፡)

  1. ሕግና የክልል አወቃቀር

አሁን ከላይ ከተነሳው ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ነጥብ በአሁን የሀገሪቱ የፖለቲካ አወቃቀር ያለው ነገርና ሕግ እንዴት ይታያል የሚለው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በፌዴራል መንግሥት፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ በሆኑ ሁለት የከተማ አስተዳደሮችና በዘጠኝ ክልሎች የተሸነሸነች ሀገር ናት፡፡ የፌዴራል ሥርዐቱ ካመጣቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ደግሞ ክልሎች የራሳቸውን የሥራ ቋንቋ መጠቀም እንደሚችሉ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሱማሌ እና ሐረሪ ክልሎች የራሳቸውን የሥራ ቋንቋ ይጠቀማሉ፡፡ አማራ፣ ቤኒሻንጉል/ጉሙዝ፣ ደ/ብ/ብ/ሕ፣ ጋምቤላ ክልሎች፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ራስ ገዝ ከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥቱ አማርኛን የሥራ ቋንቋቸው አድርገው ይጠቀማሉ፡፡

የትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሱማሌ እና ሐረሪ ክልሎች ህጎቻቸው በክልሎቹ የሥራ ቋንቋና በአማርኛ አንዳንዴ ደግሞ በእንግሊዝኛ ነው ታትመው የሚወጡት፡፡ የሕጎቻቸው ገዥ ቅጅ ደግሞ የክልሎቹ የሥራ ቋንቋ ነው-ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሱማሊኛና ሐረሪኛ/ኦሮምኛ ማለት ነው፡፡ የሌሎቹ ክልሎች እንዲሁም የሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ሕጎች ታትመው የሚወጡት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ሲሆን ገዥው ቅጅ ደግሞ አማርኛ ነው፡፡

ከላይ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው የአንዳንድ ሕጎች ተፈጻሚነት በመላ ሀገሪቱ ነው፡፡ እንደ አብነት ብንወስድ የስድስቱ ባሕረ ሕግጋት (ከአንዳድ ማሻሻያዎች በስተቀር) ተፈጻሚነታቸው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ነው፡፡ ከነዚህ አልፎም እጅግ በርካታ መሠረታዊያን ሕጎች አገር አቀፍ ተፈጻሚነት አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን አገር አቀፍ ተፈጻሚነት ያላቸውን ሕጎች በተመለከተ ክልሎች፣ የሥራ ቋንቋቸው የትኛውም ቢሆን፣ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህም ማለት እነዚህን ሕግጋት በተመለከተ ገዥው ቅጅ የአማርኛው ነው ማለት ነው፡፡ (እዚህ ላይ ግን አንዳንድ አገር አቀፍ ሕግጋት ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎማቸውን ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የ1994ቱ የወንጀል ሕግ ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሟል፤ ጥሩ ጅምር ነው፡፡)

እንደዚሁ ሁሉ ወደ ፍርድ ሥራ ስንዞር የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸው የሕግ ትርጉሞች በሁሉም ደረጃ ላይ ባሉ ፍ/ቤቶች የክልሎችን ጨምሮ ተፈጻሚነት እንዳለው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ማሻሻያ 454/1997 ደንግጓል፡፡ ይህ ችሎት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ደግሞ፣ ፍ/ቤቱ የፌዴራሉ መንግሥት በመሆኑና በይግባኝም የክልል ጉዳዮችን እየዳኘ እስከሆነ ድረስ፣ የሚጻፉትም በአማርኛ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ጉዳይ ሰፊ የሆነ ጥናትና ምርምር የሚሻ በመሆኑ በዚህ ጦማር ላይ ወደ ዝርዝር ነገሩ ጠልቀን አንመለከተውም፡፡ ሊነሳ የታሰበው ጉዳይ ቋንቋ በሕግና ፍትሕ ሥርዐት ውስጥ ምን ያህል ሚና እንዳለው ለማስረዳት ነው፡፡

  1. ሕግ ትምህርትና ቋንቋ

ታሪክ እንደሚያስረዳን ከሆነ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ በ12ኛው መ/ክ/ዘ በኢጣሊያ አገር ቦሎኛ እንደተመሠረተና በወቅቱ በዋናነት ይሠጥ የነበረው ትምህርት ደግሞ የሕግ ትምህርት እንደነበር ነው፡፡ ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በላቲን ቋንቋ ስለነበር ተማሪዎች ከየትም ይምጡ በቦሎኛ በላቲን ቋንቋ ሕግ ተምረው ወደየሃገራቸው ሲመለሱ ግን በራሳቸው ቋንቋ ያስተምሩና ይሠሩ እንደነበር ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ደግሞ ሕግ ትምህርት ዕድገቱ ተሻሽሎ፣ በአንጻሩ ደግሞ ከላቲን ቋንቋ መዳከም ጋር ተያይዞ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች መሰጠት ተጀመረ፡፡

የሮማውያንን ሕግ በዋና ምንጭነት የተጠቀመውና የሮማውያን ሕግ ቤተሰብ አባል የሆኑት የፈረንሳይና የጀርመን ሥርዐት ሕግጋት በተመቻቸላቸው የካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ሥልተ-ምርት በመጠቀም ሕጎቻቸውን ወደ ሌሎች አገሮች ለማስፋፋት በቅተዋል፡፡ በሌላኛው ገጽ ደግሞ ከ10ኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ በእንግሊዝ አገር እየዳበረ የመጣው የኮመን ሎው የሕግ ሥርዐት በተለይ በዘመነ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በመታገዝ ተደራሽነቱን በበርካታ የአፍሪካ፣ እስያና ሰሜን አሜሪካ አገሮች ለማስፋፋት በቅቷል፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዐት ከላይ ከተጠቀሰው አጭር የሕግ ሥርዐት ታሪክ ጋር የሚዛመድ ነገር አለው፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም ታሪኳ ለኮንቲኔንታል ሕግ ቅርበት ያለው በመሆኑ በዋናነት የፈረንሳይን የሕግ ሥርዐት እንድትከተል አስችሏታል፡፡ ፈረንሳይኛ ለባሕረ ሕግጋቱ ዋና ምንጭነት የሆነው፣ ፈረንሳይኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ የሕግ ት/ቤቶች በአማራጭነት እንዲሰጥ የሆነበት አንድምታ በዚሁ የታሪክ ሰንሰለት ተያይዞ ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ነገር ከላይ ስለተመለከተ እዚህ ላይ መድገሙ ተገቢ አይደለም፡፡

በዚህ ሁሉ የታሪክ ዑደት ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ጉዳይ መግባቢያ ሆኖ ሲያገለግል የኖረው አማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ ከፌዴራሊዝም ሥርዐት በፊትም ሆነ በአሁኑ ወቅት በፌዴራሉም ሆነ በክልሎች ውስጥ ሕግ የሚወጣው ከላይ እንደተብራራው በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በክልል የሥራ ቋንቋዎች እንደሆነ አይተናል፡፡ የራሳቸውን ቋንቋ የሚጠቀሙትን ክልሎች ጉዳይ ብቻ የተመለከተ ካልሆነ በስተቀር በክልሎችም ቢሆን ገዥው ቋንቋ አማርኛ እንደሆነም ተረድተናል፡፡ በአንጻሩም የፍትሕ ሥርዐቱ ዋና የሰው ሃይል መጋቢ ሆነው የሚያገለግሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሕግ ት/ቤቶች የሕግ ትምህርትን የሚያስተምሩት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ ትምህርት በእንግሊዝኛ ሥራ ደግሞ በአማርኛ እንደሆነ ጠቅላላ ነገር እንውሰድ፡፡

ሕግ ከሌሎች የትምህርት መስኮች የተለየ የራሱ የሆነ ልዩ የቋንቋ አጠቃቀምን (Jargon) የያዘ የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ በየትኛውም ቋንቋ የሕግ ትምህርት ቢሰጥ ከቋንቋው ልዩነት ውጭ አንድ የሚያደርገው ነገር አለ፡፡ እዚህ ላይ ቋንቋ ስል የሕግ ቃላት፣ ሐረጋትና አጠቃቀማቸው ከሥርዐተ ነጥቦቻቸው ለማለት እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ በሕግ ትምህርት ውስጥ ቃላት እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ነው ያላቸው፤ ምክንያቱም ሕግ ማለት የእያንዳንዱ ቃል ድምር እና የሕግ ትርጉም ማለት ደግሞ ቃላትን መተርጎም ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ተራ የቃል ትርጉም ሳይሆን ሕግ በሚያዘው መሠረት፣ የሕጉን መንፈስ በተከተለ መልኩ መተርጎም ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጥሩ የሕግ ቋንቋ ችሎታ ለሕግ ትምህርት፣ ትርጉም፣ አፈጻጸም ያለው ድርሻ የጎላ ነው፡፡

ይቀጥላል…፡፡

[1]

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s