‹‹የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በሕዝብ ሉአላዊነት እንጅ በመሬት ሉአላዊነት ላይ የተገነባ አይደለም፡፡›› (ጠ/ሚ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ)

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ጠ/ሚ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡትን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ተከታትየዋለሁ፡፡ ከም/ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከም/ቤቱ አባላት መካከል የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጭ የሆኑት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ብዙ ጥያቄ ሲጠይቁ አይተናል፡፡ ከ99% በላይ የገዢው ፓርቲ አባል ተመራጭ በተቆጣጠሩት ም/ቤት ለአንድ ግለሰብ ይህን ያክል ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ መፈቀዱ የምር ጥሩ ነገር ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ሌሎች የም/ቤቱ አባላትም ሕዝብን ወክለው፣ የሕዝብን ጥያቄ ሊያቀርቡ፣ ሊወስኑ ነው የተመረጡትና የተሰየሙት፡፡

ዋናው ጉዳይዬ ከአቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄዎች መካከል በአንዱ ጥያቄ ላይ እና ጠ/ሚኒስትሩ ለጥያቄው የሰጡትን መልስ በተመለከተ ነው፡፡ አቶ ግርማ ዳር ድንበር አካባቢ ስላለው ኢንቨስትመንትና ስለ ኢትዮጵያ ሉአላዊነት አንድ ነጥብ አንስተው ጠ/ሚኒስትሩም በበኩላቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ (ጥያቄው በጋምቤላ ክልል የሚያጠነጥን ይመስላል፡፡) በተለይም አቶ ግርማ ስለውጭ አገር ባለሃብቶችና ስለድንበር አካባቢ ያለው የኢትዮጵያ ሉአላዊነት፣ ኢንቨስትመንቱ በሉአላዊነታችን ላይ ሊያደርሰው ስለሚችለው ሥጋት ወይም አሉታዊ ጎን ቆም ብለን እንድናጤነው የሚያሳስብ ጥያቄ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡
ከዚህ በላይ ለቀረበው ጥያቄ የጠ/ሚኒስትሩ መልስ በአጭሩ ‹‹የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በሕዝብ ሉአላዊነት ላይ እንጅ በመሬት ሉአላዊነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የጋምቤላ ሕዝብ በራሱ ክልል ውስጥ ሉአላዊ ነው፡፡ የክልሉ ሕዝብ የራሱን ሉአላዊነት አሳልፎ ይሰጣል ብለን አንገምትም፡፡ …›› የሚል ነው፡፡ ከዚህ የጠ/ሚኒስትሩ መልስ አንዳንዱ መሠረት የያዘ እውነት ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ ግራ የሚያጋባ፣ የተድበሰበሰ እና ግልጽነት የሚጎድለው ነው፡፡

የጋምቤላ ሕዝብ በራሱ ክልል ሉአላዊ ስለመሆኑ የተነገረው እውነታ ስለሆነ ትንታኔ የሚያስፈለገው አይደለም፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች (ብ/ብ/ሕ) በራሳቸው ክልል ውስጥ ሉአላዊ የሥልጣን ባለቤት ናቸው፡፡
በአንጻሩ ጠ/ሚኒስትሩ ስለ ሉአላዊነት የመለሱት መልስ ብዙ አንድምታ ያለውና ለትንታኔም ሆነ ለሙግት የሚጋብዝ ነው፡፡ እስኪ የጠ/ሚኒስትሩን መልስ አንድምታውን እንመርምረው፡፡

ሉአላዊነት በራስ ጉዳይ ላይ ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ የመስጠት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የመከልከል፣ በውጭ አካል ያለመደፈር፣ የሚሉ ነገሮችን ያካትታል፡፡ የሕዝብ ሉአላዊነት ስንል በራስ (ውስጥ) ጉዳይ ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ የመስጠት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የመከልከል፣ የማስወገድ የሚያካትት ነው፡፡ የሕዝብ ሉአላዊነት በራስ ጉዳይ ላይ ፍጹም የሆነ ሥልጣን አለው፡፡

የመሬት ሉአላዊነትስ ምንድን ነው? መሬት ስንል በተለምዶ የምንቆምበትን መሬት ማለት ብቻ ሳይሆን የአንድን አገር ግዛት (Territory) ለማለት ነው፡፡ በትርጉም ረገድ ‹‹መሬት›› ስንል በቁሙ ‹‹ግዛት›› ከሚለው ቃል አንጻር ሲታይ ጠበብ ያለ ቃል ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ግዛት ስንል የብሱን፣ የአየር ክልሉን፣ የውሃ አካሎችን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ መሬት የሚለውን ሰፋ ባለ ትርጉሙ ግዛት ብለን እንረዳው፡፡ የመሬት ሉአላዊነት ሰፋ ባለ ትርጉሙ ‹‹የግዛት ሉአላዊነት›› (Territorial Sovereignty) ለማለት እንደሆነ ግንዛቤ እንውሰድ፡፡ የግዛት ሉአላዊነት በራስ ግዛት ላይ የፈለጉትን የማድረግ እና ግዛትን ከውጭ ጥቃትም ሆነ ወረራ የመከላከል መብትን ያጎናጽፋል፡፡

ስለዚህ የሕዝብ እና የግዛት ሉአላዊነት የሌለው መንግሥት አይኖርም፡፡ አንድ መንግሥት የሕዝብ እና የግዛት ሉአላዊነት የሌለው ከሆነ ወይም ከሁለቱ አንዱ የሚጎድለው ከሆነ ከመጀመሪያውኑ ነጻ መንግሥት አይደለም፤ ወይም መንግሥትነት የለውም፤ ወይም ለመንግሥትነት ብቁ አይደለም፡፡ ሁለቱም በአንድነት ሊኖሩት ይገባል፡፡ የሕዝብ ሉአላዊነት ያለ ግዛት ሉአላዊነት አይኖርም፤ የግዛት ሉአላዊነትም ያለ ሕዝብ ሉአላዊነት ሊኖር አይችልም፡፡ አንዱን ያለ አንዱ ልናስብ እና ነጥለን ልንናገር ከቶ አይቻለንም፡፡ ሕዝብ ብቻ እያልን ግዛትን፣ ግዛት ብቻ እያልን ሕዝብን ልንተው አንችልም፡፡ ስለ ሕዝብ እያልን ግዛቱን ካልጠበቅንለት፣ ስለ ግዛት እያልን ሕዝቡን ካልጠበቅንለት የቱ ላይ ነው ሉአላዊነቱ? ባለፉት ታሪካችን፣ ሁል ጊዜም ባይሆን እንኳ አንዳንድ ጊዜ፣ ሁለቱንም በአንድ ላይ ማየት አቅቶን ግዛትን ስንል ሕዝብን፣ ሕዝብን ስንል ግዛትን አጥተናል፡፡ ሲከፋ ደግሞ ስለ ሁለቱም ማሰብ አቅቶን ሁለቱንም ያጣንባቸው ታሪኮችም አሉን፡፡ ሕዝብ የራሱም ሆነ የግዛቱ ሉአላዊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ አለዚያ ግን ግማሽ ሕይወት ነው፡፡

ኢትዮጵያን በታሪኳ የገጠሟት የሕዝቧንና የግዛቷን ሉአላዊነት ሊገፉ የመጡ ባእዳን ወራሪዎችን እናስታውሳለን፡፡ እነዚህ የውጭ ወራሪዎች የኢትዮጵያን የሕዝቧንና የግዛቷን ሉአላዊነት የሚጨፈልቁ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ታሪካችን እነዚህን ባእዳን ስንዋጋ ዓላማችን የነበረው የራሳችንም ሆነ የግዛታችን ሉአላዊነት ለማስከበር ነው፡፡ እርስ በርሳችንም ስንዋጋ ከራሳችን ሉአላዊነት አልፎ የግዛት ሉአላዊነታችን ያጣንባቸውን ክስተቶችም አንዘነጋም፡፡ በቃ ምን አደከመኝ፣ ሉአላዊነት ለአንድ አገር ከምንም በላይ ነው!! ለኛ ለኢትዮጵያውያንም እንዲሁ!! ሕዝባችንም ግዛታችንም ተደፍሮብን ስለቀመስነው ይሄው እስከ አሁን ድረስ ህልውናችን ሉአላዊነታችን፤ ሉአላዊነታችንም ህልውናችን ነው፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያን ሕዝብ ከግዛቱ፣ የኢትዮጵያን ግዛትም ከሕዝቡ ለያይትን ልናስብ ፈጽሞ ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ እናም ወደ ጠ/ሚ ሃይለ ማርያም መልስ ልመለስ፡፡ ‹‹…የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በሕዝብ ሉአላዊነት ላይ እንጅ በመሬት ሉአላዊነት ላይ የተመሠረተ አይደለም…፡፡›› ክቡር ጠ/ሚ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት የሁለቱም ድምር ውጤት እንጅ የግዛት ሉአላዊነት ከሕዝብ ሉአላዊነት ተነጥሎ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሕዝቤ እስካልተነካ ድረስ በግዛቴ ላይ የፈለገው ይሁን ብለን ልንናገር ቀርቶ ልናስብ እንችላለን? በግዛታችን ላይ በኛ ላይ ሴራ ቢሸረብ፣ ወንጀል ቢፈጸም፣ ግዛታችን ቢነጠቅ፣ ቢደፈር … የራሱ ጉዳይ ልንል ነውን? በግዛቱ ላይ ማናቸውንም አይነት ነገር የመቆጣጠር ሥልጣን እኮ የሕዝብ ሉአላዊነት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በግዛቴ ውስጥ የሕዝብ ሉአላዊነቴ እስካልተነከ ድረስ የፈለገው ይሁን ማለት እኮ ሕዝቡ በዚያ ግዛት ላይ ምንም ዓይነት ሉአላዊነት የለውም ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደዚህ የምንል ከሆነ ስለ ግማሽ ሉአላዊነት፣ ስለ ግማሽ ሕይወት እያሰብን እየኖርን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብ ሉአላዊነት እየተሸራረፈ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የአንዱ መደፈር የሌላውንም መደፈር ስለሚያስከትል ነው፤ ማለትም የግዛት ሉአላዊነት መደፈር የሕዝብ ሉአላዊነት መደፈርን፣ በተቃራኒውም የሕዝብ ሉአላዊነት መደፈር የግዛት ሉአላዊነት መደፈርን ያስከትላል፡፡ ደግሞስ ‹‹ዳሩ ካልተጠበቀ፣ መሃሉ ዳር ይሆናል፡፡›› የሚለውን ብሂል እንደምን ልንዘነጋው እንችላለን?

ይልቁንስ እነዚህን የውጭ ባለሃብቶች በአገራችን ላይ ገንዘባቸውን አፍስሰው ሲሰሩ የሚገባውን ቁጥጥር ልናደርግ ይገባናል፡፡ ይህ ቁጥጥራችን የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የገንዘብም ሆነ የካፒታል ፍሰት የሚገድብ አይምሰለን፡፡ የትም አገር ቢሆን የውጭ ባለሃብቶች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ዕድል የለም፤ እነሱም ያውቁታል፡፡

ይህን ነገር ለመገንዘብ ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገቸውን ነገር ማስታወስ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ፈረንሳይና ኢትዮጵያ ከጅቡቲ-አዲስ አበባ የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋት ውል ተዋውለው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በመጨረሻ ፈረንሳዮች ሲወጡ ጅቡቲን ምን እንዳደረጉ የብዙ ክ/ዘመን ሳይሆን የግማሽ ክ/ዘመን የወደ ኋላ ታሪካችን ይነግረናል፡፡

እስኪ ደግሞ ‹‹የጋምቤላ ክልል ህዝብ የራሱን ሉአላዊነት አሳልፎ ይሰጣል የሚል እምነት የለኝም›› በማለት ጠ/ሚ የሰጡትን መልስ ጥቂት እንመርምር፡፡ ከዚህ መልስ ላይ ሁለት ነገሮችን ነቅሰን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ለዘብ ያለ ሆኖ የክልሉ ሕዝብ ሉአላዊነቱን አሳልፎ ቢሰጥ የራሱ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም ለማለት ይሆን? ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ አንድ ክልል ያለው ሉአላዊነት እስከ ምን ድረስ ነው? የግዛት ሉአላዊነቱንስ እስከ ምን ድረስ ነው ሊጠቀምበት የሚችለው የሚለው ነው፡፡ በመሠረቱ አንድ ክልል በራሱ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ሉአላዊነት ቢኖረውም እንኳ ያንን ግዛት አሳልፎ የመስጠት ሥልጣን በየትኛውም ሕግ አልተሰጠውም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የፌዴራሉ መንግሥት የአንድን ክልል የግዛት ሉአላዊነት በራሱ አሳልፎ የሚሰጥበት ሥልጣን የለውም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአንድ ክልል ሉአላዊነት ሌሎች ክልሎችንም ይመለከታቸዋል፡፡ ለምሳሌ ብንመለከት የአንድ ክልል የግዛት ሉአላዊነት ሌሎች ክልሎችንም ይመለከታቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ክልሎች በፌዴራል መንግሥቱ ተሳስረዋልና ነው፡፡ ደግሞም እኮ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 2 እንደሚለው ከሆነ የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራል አባል ክልሎችን ወሰን የሚያጠቃልል ስለሆነ የአንድ ክልል የግዛት ሉአላዊነት መደፈር የሌሎች ክልሎችም መደፈር ነው፡፡ ለዚያ አይደል እንዴ የምሥራቅ ወይም የሰሜን የግዛት ወሰን ሲደፈር ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ሆ ብሎ ለሉአላዊነቱ የሚነሳውና የሚያስጠብቀው፡፡

ሕገ መንግሥቱም ቢሆን፣ አይደለም ለክልሎች ይቅርና ለፌዴራል መንግሥቱም ቢሆን የግዛት ሉአላዊነትን አሳልፎ የሚሰጥበት ሥልጣን አልሰጠውም፡፡ ይህን ጉዳይ በዋናነት ያነሳሁት ጠ/ሚ የሰጡትን መልስ ለመፈተሽ እንጅ ድርጊቱ ተፈጽሞ ወይም ደግሞ ጥያቄው ተነስቶ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የሚገባበት ምክንያቶች በሕገ መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/95 ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት በክልሎች ውስጥ የግዛት ሉአላዊነትን የሚጎዳ ድርጊት ሲፈጸም የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ በጋምቤላ ክልል የውጭ አገር ባለ ሃብቶች የዳር ድንበር አካባቢ ሉአላዊነት የሚጥሱ ነገሮችን እየፈጸሙ እንደሆነ፣ ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ድርጊትን አመላካች ነገሮች ቢኖሩ፣ ከሕገ መንግሥቱን ከሌሎች አግባብ ካላቸው ሕጎች አንጻር መታየት አለበት እንጅ ‹የክልሉ ሉአላዊነት እስከሆነ ድረስ እኛ ምን አገባን› ዓይነት የመሰለ የተድበሰበሰ መልስ አይጠበቅም፡፡

የውጭ አገር ባለሃብቶች ሥራቸውን ስንመለከት ሰፊ የልማት ቦታ በተለይ በጋምቤላ ክልል ተሰጥቷቸው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባለሃብቶች ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችሉ ስለመሆናቸው፣ አንዳንዴም መንግሥት የማስገልበጥና ሕዝባዊ ብጥብጥ ማስነሳት የሚችሉ እንደሆነ በአንዳንድ አገሮች ታይቷል፡፡ ይህም እነዚህ ባለሃብቶች የራሳቸው የሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዓላማ ስላላቸው ጭምር ነው፡፡ ባገራችን የሚገኙትም ምንም እንኳ ጥንካሬያቸው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በቅርብ ባላውቅም ከላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት እኩይ ግብር ሊኖራቸው ስለሚችል አስፈላጊውን ክትትል ማድረጉ ይበጃል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለጥቅሙ እንደምንጓጓ ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለውም አውቀን ልንጠነቀቅ ይገባል እላለሁ፡፡

ስለዚህ የአቶ ግርማ ጥቆማ ቸል የምንለው ጉዳይ ሳይሆን ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት የሚገባን ነገር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የግዛት ሉአላዊነትን ነገርም ላላ አድርገን ባንመለከተው ይበጃል፤ ጊዜውን ጠብቆ የምንጠነቀቅለትን የሕዝብ ሉአላዊነት ሰንጎ የሚይዝ ጉዳይ ነውና! የግዛት ሉአላዊነት ለቀቅ አድርገን የምንገነዘበው ከሆነ ወደ ፊት ለህልውናችን አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s