ስለ መጓጓዝ ውል (Contract of Carriage)

Image

 

ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ነገር ብዙውን ጊዜ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ ሳስብ ከአሽከርካሪዎችና ከረዳቶቻቸው ጋር የሚገጥመኝ (ምናልባት ሁላችንንም የሚገጥመን) ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በርካታ ጊዜ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ ጉዞ ስናደርግ የሚገጥሙን አምባ ጓሮ መቼም ቢሆን ጉዞ አድርጎ የሚያውቅ ሰው የሚጠፋው አይደለም፤ ሁላችንም ስለሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ፡- በተጠቀሰው ሰዓት አለመነሳት፣ ከተተመነው ተመን (Tariff) በላይ ማስከፈል፣ የማያስከፍሉ እቃዎችን/ጓዞችን ማስከፈል፣ ከሚገመተው በላይ ማስከፈል፣ በቂ ምግብ በሌለበት ቦታ ማሳረፍ፣ ከተፈቀደው የጉዞ ሰዓት ውጭ በማሽከርከር ተሳፋሪዎችን በምሽት ማንገላታት/እንደ ጉዞው ርቀት መኝታ ሊያጡም ይችላሉ/፣ ባልተፈለገ ቦታና ሰዓት ተሸከርካሪን በማቆም ተሳፋሪን ማንገላታት፣….

አንድ ጊዜ ከሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ያጋጠመኝን ነገር ላውጋችሁ፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ አሽከርካሪው ያለምንም ምክንያት (ወይም ለግል ጥቅሙ በማሰብ ብቻ) መኪናውን በየመንገዱ ማቆም አበዛ፤ ሰው ሰላም ለማለት፣ አንዳንድ ጊዜ ለሆድ፡፡ ለመናፈስ፣ ቁርስም ሆነ ምሳ ለመብላት ከሆነ ሁሉንም ተሳፋሪ ተናግሮ ማቆም ነበረበት፡፡ ምክንያቱም በጉዞ ወቅት ተሳፋሪዎች በቂ ምግብ ካለበት ስፍራ የመመገብ፣ በቂ መኝታ ካለበት ቦታ የማደር፣ … ሙሉ መብት አላቸው፡፡ ይህ የመጓጓዝ ውሉ የሰጣቸው መብት እንጅ እንዲሁ አሽከርካሪው ሲፈልግ የሚሰጣቸው ሲያሰኘው ደግሞ የሚነፍጋቸው አይደለም፡፡

እኔም በአሽከርካሪው ድርጊት ጥቂት ንዴት ቢጤ ተሰምቶኝ “እባክህን ለቁርስ ወይም ለመናፈስ ከሆነ እኛም እንውረድ፣ አለዚያ ለምንድን ነው ያለ ምክንያት በየቦታው የምትቆም? በጊዜ መግባት እንፈልጋለን” ብዬ ተናገርኩት፡፡ አሽከርካሪው እንደ ገነፈለ ድስት ቱግ ብሎ “ከፈለግህ ኮንትራክት ይዘህ መሄድ ትችላለህ፤ በኮንትራክት የምትሄድ መሰለህ፤ ከፈለክ ደግሞ አንተ ንዳው” ብሎ ደነፋብኝ፡፡ የምጓዘው ውል (ኮንትራክት) ገብቼ ፈቅዶ፣ ፈቅጄ፣ መሆኑን ላስረዳው አስቤ ግን በዚያ ድንፋቱ ላይገባው ብዬ ተውኩት፡፡ ዳሩ እዚች አገር መብት መጠየቅ ሞኝነት አይደል!! መብት የሚገኘው/የሚከበረው በጭቅጭቅና በደጅ ጥናት ነው፡፡ ለማንኛውም ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል እንደሚባለው ሁሉ ተናግሬ በመጠኑ አስተካከለ፤ በኋላ ሳይገባው አልቀረም፡፡

በዚህ መነሻነት እስኪ ስለ መጓጓዝ ውል እንጨዋወት፡፡ ታዲያ እንደማመጥ፡፡

በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት ሦስት ዓይነት የመጓጓዣ መንገዶች አሉ፤ የመሬት፣ የአየርና የውሃ፡፡[1] ይህም ሦስት የመጓጓዝ ውል ዓይነቶች አሉ ማለት ነው፡፡ የአየሩን መጓጓዣ ከአንድ ጊዜ በላይ ስላልተጠቀምኩበት፣ የውሃውንም ተጠቅሜበት ስለማላውቅ ለጊዜው ወደ ጎን ልተዋቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነገራቸውን እግረ መንገዳችን እናያለን፡፡ ዋና ትኩረቴን እስከ አሁን ድረስ የሁል ጊዜዬ በሆነው በመሬት ላይ ስለመጓጓዝ አደርጋለሁ፤ በተለይም በመንገድ ላይ ስለሚደረግ የመጓጓዝ ውል፡፡

በመሬት ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ማለት ‹‹ዋጋ በመቀበል ሰዎችን፣ ጓዝን (Baggage) ወይም ዕቃዎችን (Good) በመሬት ላይ የተዘረጋ በተለይም በመንገድ፣ በምድር ባቡር መንገድ ወይም በመሬት መሓል በሚገኙት ዥረቶች፣ ወንዞች፣ ቦዮች ወይም ሐይቆች ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ነው፡፡››[2] በዚህም መሠረት በአውቶቡስ፣ በታክሲ፣ በባጃጅ፣ በብስክሌት፣ በባቡር ወይም በነጣና በነሀዋሳ በነቢሾፍቱ እና በሌሎችም ሐይቆች ላይ በጀልባ የሚደረግ ሰውን ወይም ጓዝን ወይም ዕቃን ማጓጓዝ፣… በመሬት ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል እንለዋለን ማለት ነው፡፡

በአየር ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ደግሞ በንግድ ሕጉ ከቁጥር 604-653 ባሉት የሚገዛ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቪየሽን አዋጅ ቁጥር 616/2001 ለዚህ ዓይነት የመጓጓዝ ውል ተገቢ የሆነ ሕግ ስለሆነ ከንግድ ሕጉ ቁጥሮች ጋር አብሮ መታየት አለበት፡፡ ይህም በአውሮፕላን የሚደረግ በአጓጓዡ እና በተጓዡ ሰው፣ ጓዝ ወይም ዕቃ የማጓጓዝ ውል ነው፡፡ በውሃ ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ደግሞ የሚገዛው በባሕር ሕግ መሠረት ነው፡፡ እንዲሁም የመልቲ ሞዳል አዋጅ ቁጥር 548/1999 በባሕር ላይ የሚደረግ የማጓጓዝ ውልን ለማስተዳደር ስለሚያገለግል ከባሕር ሕግ ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ይህም በመርከብ የሚደረግ በአጓጓዡ እና በተጓዡ ሰው፣ ጓዝ ወይም ዕቃ የማጓጓዝ ውል ነው፡፡ አስቀድሜ እንደጠቆምኩት ትኩረቴ በመሬት በሚደረገው በተለይም በመንገድ የመጓጓዝ ውል ላይ ነው፡፡

ስለ ሁሉም ዓይነት የመጓጓዝ ውሎች ስናነሳ ምንጊዜም ጓዝ እና ዕቃ የሚሉ ቃላት አይለዩም- የውሉ አካላት ስለሚሆኑ፡፡ ነገር ግን የሁለቱ አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው? የሁለቱ ቃላት ትርጓሜ በንግድ ሕጉም ሆነ በባሕር ሕጉ ላይ አልተነገረም፡፡ የነዚህን አንድ የሚመስሉ ነገር ግን ልዩነት ያላቸው ቃላት ትርጓሜ ለመረዳት የንግድ ሕጉን ጠለቅ ብሎ መመርመር ይጠይቃል፡፡ ልዩነት እንዳላቸው የምንረዳው ሁለቱ ቃላት በተለያዩ የንግድ ሕጉ ክፍሎች ለብቻቸው ስለተጠቀሱ ነው፡፡ ቁጥር 568-569 ያሉት የንግድ ሕጉ ቁጥሮች ስለ ጓዝ የሚናገሩ ናቸው፡፡ በአንጻሩም ከቁጥር 570-586 ያሉት የንግድ ሕጉ ቁጥሮች ስለ ዕቃ የሚናገሩ ናቸው፡፡

 

በዚህም መሠረት የንግድ ሕጉን ቁጥር 567 እና 568 በጥልቀት ስንመለከታቸው ‹‹ጓዝ›› ሲል አንድ ተጓዥ ሲጓዝ አብሮ ይዟቸው የሚሄዱ ንብረቶችን ለማለት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአንቀጽ 567 ላይ ለጓዝ የሚከፈል ዋጋ ከመንገደኛው ሰው ዋጋ ጋር አብሮ ሊከፈል እነደሚችል ይጠቁማል፤ እንዲህ በማለት ‹‹…በመንገደኛው የመጓጓዣ ዋጋ ላይ የተጨመረ ካልሆነ በቀር…››፡፡ ይህ ጓዝ ማለት መንገደኛው አብሮ ይዟቸው የሚጓዙ መሆናቸውን በግልጽ ይነግረናል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በታች ባለው አንቀጽ እንደማብራራው ለጓዝ ትኬት መንገደኛው ከፈለገ አጓጓዡን ሊጠይቅ ይችላል፤ ካልፈለገ ደግሞ ይተወዋል፡፡

 

የንግድ ሕጉ ‹‹ዕቃ›› ሲል ደግሞ አንድ ሰው እርሱ መጓዝ ሳያስፈልገው የሚልከውን ዕቃ ከአጓጓዡ ጋር በመስማማት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚልካቸውን ንብረቶች ለማለት ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ደግሞ ሕጉ ‹‹ላኪ›› እና ‹‹ተቀባይ›› የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ ስለሚጠቀም ይህንን ማስተዋሉ በቂ ነው፡፡ ላኪና ተቀባይ አለ ማለት ላኪው ሰው ከዕቃው ጋር የሚሄድ አለመሆኑን ነው፡፡ የንግድ  ሕጉ ከቁጥር 577-582 ድረስ ስለ ላኪና ተቀባይ አብራርቶ ይናገራል፤ ከመብትና ግዴታዎቻቸው ጋር፡፡ እንደ ጓዝ ትኬት ሁሉ የዕቃ ማጓጓዣ ሰነድ (Consignment Note) አለ፡፡ (በአውሮፕላን የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ሲሆን ደግሞ የአየር ማጓዣ ሰነድ (Bill of Lading) ይባላል፡፡) ይህን ሰነድ አጓጓዡ ላኪውን የመጠየቅ ላኪውም አጓጓዡ እንዲቀበለው የመጠየቅ መብት እንዳለው ቁጥር 571 በግልጥ ይናገራል፡፡ እንዲያውም የዕቃ ማጓጓዣ ሰነድን የሚመለከቱት የንግድ ሕጉ ቁጥሮች የጓዝ ትኬትን ከሚመለከቱት ቁጥሮች እጅግ በዛ እና ጠንከር ብለው እናያቸዋለን፡፡[3] እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የዕቃ ማጓጓዣ ሰነድ ሊኖር ግድ የሚል ይመስላል፡፡

 

‹‹ዕቃ›› የሚለው ቃል ተተርጉሞ የምናገኘው በመልቲ ሞዳል አዋጁ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ዕቃ ማለት ‹‹ማንኛውም ንብረት ሆኖ የቁም ከብቶችን፣ እንዲሁም ኮንቴይነሮችን፣ የዕቃ ማሸጊያ ሳጥን (Pallets) ወይም ተመሳሳይ ዕቃ የሚታሸግበት ወይም በዕቃ አስረካቢው የሚሰጡ ማናቸውም የዕቃ ማሸጊያዎችን ይጨምራል፡፡›› በማለት በአንቀጽ 2(7) ሥር ተተርጉሟል፡፡ አዋጁ ዕቃ የሚለውን ቃል የተረጎመው በባሕር ላይ ስለሚደረግ የመጓጓዝ ውል ዐውድ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ውስጥ ላኪ እና ተቀባይ የሚሉት ነገሮች በስፋት ተካተው ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጅ ‹‹ዕቃ›› ማለት አንድ ሰው እርሱ ከዕቃው ጋር መጓዝ ሳያስፈልገው ወይም ዕቃው ከእርሱ ጋር መጓዝ ሳያስፈልገው በአጓጓዡ አማካኝነት የሚልከው ንብረት እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

 

ዳግመኛ ወደ ዋናው ነገራችን እንመለስ፡፡

በፍትሐ ብሔሩ አጠቃላይ የውል ሕግ ድንጋጌዎች እንደተነገረው ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡[4] ይህ አጠቃላይ የውል ትርጉም ሲሆን እያንዳንዱ የውል ዓይነት ደግሞ እንደየሁኔታው ይተረጎማል፡፡

በዚህም መሠረት የማጓጓዝ ውል ማለት አጓጓዥ ዋጋ በመቀበል ሰውን፣ ጓዝንና ዕቃዎችን እተወሰነ ስፍራ ለማድረስ ግዴታ የገባበት ስምምነት ነው፡፡[5] ይህ ማለት በማጓጓዝ ውል ውስጥ አጓጓዥ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሚጓዝ ሰው፣ ወይም ጓዝ፣ ወይም ዕቃ፣ ወይም ሁለቱ፣ ወይም ሁሉም በአንድ ላይ አለ ማለት ነው፡፡ ውል እስከሆነ ድረስ በአጓጓዡ ሰው እና በተጓዡ ሰው (ወይም ዕቃዎቹ) መካከል ስምምነት አለ፡፡ እርሱም ገንዘብ የተከፈለበት ነው፡፡ በመጓጓዝ ውል ውስጥ የአጓጓዡ ዋናው ግዴታ ተጓዡን ሰው ወይም ጓዙን ወይም ዕቃውን ወይም ሁሉንም በአንድ ላይ እተወሰነ ስፍራ ማድረስ ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት ይህ ውል ገንዘብ የተከፈለበት ነው፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ ላይ የሚደረገው የመጓጓዣ ዋጋ የሚወሰነው በመንግሥት ነው፡፡ በዚህም መሠረት የከተማ ታክሲ፣ የአጭርና የመካከለኛ እንዲሁም የረጅም ርቀት (አገር አቋራጭ) የመንገድ መጓጓዝ ዋጋን የሚተምነው መንግሥት (መንገድ ትራንስፖርት) ነው፡፡[6]

በመንገድ ላይ በሚደረግ የመጓጓዝ ውል ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች በዋጋ ላይ አይደራደሩም፡፡ ምክንያቱም በመንገድ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ዋጋው በመንግሥት የሚተመን ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እንደሚታወቀው ተጓዡ ሰው ከአጓጓዡ ላይ በመንግሥት የተተመነውን ዋጋ ከፍሎ የጉዞ ትኬቱን ይቆርጣል/ይገዛል፡፡ (ይህም የመንገደኞች ትኬት የሚባለው ነው፡፡[7]) በርግጥ በንግድ ሕጉ ቁጥር 567(1) እንደተጠቀሰው ትኬት መቁረጥ ግዴታ አይደለም፡፡ አጓጓዡ ትኬት እንዲቆረጥ የፈለገ እንደሆነ ግን ተጓዡ ትኬት መቁረጥ ይኖርበታል፡፡ እንደሚታወቀው በአብዛኛው የረጅም እና የመካከለኛ ርቀት ጉዞ ሲኖር ነው ትኬት የሚቆረጠው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ አንበሳ አውቶቡስ ያሉ የከተማ ውስጥ የመጓጓዝ ውል ተጓዥ ሰው ትኬት የመቁረጥ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የሆነውም አጓጓዡ ትኬት እንዲቆረጥ ስለፈለገና ስለሚያስገድድ ነው፡፡ ይህም ከፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 567(1) ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ስለዚህ ትኬት መቁረጥ በአጓጓዡ ፍላጎት ላይ የተወሰነ ነው ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ የምንረዳው የመጓጓዝ ውል ለመመሠረት ትኬት መቁረጥ ግዴታ አለመሆኑን ነው፡፡[8]

የመጓጓዝ ውል ለመመሠረት ትኬት መቁረጥ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሚቀድመው የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ነው፡፡ ትኬት ለውሉ ማስረጃ የሚሆን ሰነድ ነው፡፡ የመጓጓዝ ውል ተመሠረት የሚባለው አጓጓዡና ተጓዡ ሲስማሙ ብቻ ነው፡፡[9] በዚህ ጊዜ ሁለቱ ወገኖች ውል ስለተዋዋሉ መብትና ግዴታቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይመነጫል፡፡ ውሉ ከተመሠረተ በኋላ ያለው ጉዳይ ስለ ውሉ አፈጻጸም የሚመለከት ነው፡፡

በመንገድ ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ሌላው ገጽታ ስለ ጓዝ ትኬት የሚመለከት ነው፡፡[10] ለመንገደኞች ትኬት አጓጓዡ ለተጓዡ ሰው ትኬት እንዲይዝ ለማድረግ (ለማስገደድ) እንደሚችለው ሁሉ፣ ለጓዝ ትኬት ደግሞ ባለ ጓዙ ሰው አጓጓዡን ትኬት እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል፡፡[11] ነገር ግን ለጓዝ የሚከፈለውን ዋጋ መንግሥት የሚተምነው ሳይሆን ተዋዋይ ወገኖች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ በውል እንደሚታወቀው (በአብዛኛውም ከመንገደኛ ትኬት ጀርባ ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው) ከ25 ኪሎ ግራም በታች ለሆነ ዕቃ ወይም ጓዝ ዋጋ አይከፈልም፡፡[12] መንቻካ ሹፌርና ረዳት ከገጠመው ግን በአብዛኛው የጓዙ ወይም የዕቃው ባለቤት የመደራደር አቅም ስለማይኖረው መክፈል አይቀርለትም፡፡ ምናልባት በሚከፈለው መጠን ላይ ይደራደር ይሆናል፡፡ በሕግ ውስጥ ሊያስከፍሉ ስለሚችሉ እና ስለማይችሉ ጓዞች ወይም ዕቃዎች በግልጽ የተነገረ ነገር የለም፡፡[13]

ከዚህ ባለፈ ከዚህ ላይ አንድ ዋና ነጥብ ሊነሳ ግድ ይላል፡፡ ይኸውም ምንም እንኳ በመንገድ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ዋጋ/ተመን በመንግሥት የሚወጣ ቢሆንም ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ከዚህ ተመን በላይ ወይም በታች ሊስማሙ ይችላሉ፡፡[14] ይህ ውልን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህም ውል በሁለቱ ወገኖች መካከል በፈቃደኝነት የሚደረግ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱም የውል ጽንሰ-ሀሳብ ዋና መርህ የሆነው “የመዋዋል ነፃ ፈቃድ”/Freedom of Contract/ የሚባለው ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረት የተዋዋይ ወገኖች ውል አስገዳጅ ሕግን ወይም የተዋዋይን ነፃ ፈቃድ ወይም ልዩ የሆነ የውልን ፎርም ወይም ሞራልን እንካልተቃረነ ድረስ እንደፈቀዱ እንዲዋዋሉ ያስችላቸዋል፡፡

ይህንን ለማስረዳት አንድ ማብራሪያ ላቅርብ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደምናስተውለው ተጓዦች ወደ አንድ ስፍራ ለመሄድ ሲያስቡ በተለምዶ “በኮንትራክት” እንሂድ ይባላል፡፡ ለምሳሌ፣ በበዓላት ሰሞን፣ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ተማሪዎች ሲገቡና ሲወጡ፣ ለተለያዩ መደበኛ ላልሆኑ ጉዞዎች /እንደ ጉብኝት፣ መንፈሳዊ ጉዞ…/፣ … ተጓዢ ስለሚበዛ “በኮንትራክት” እንሂድ ይባላል፡፡ የኮንትራክት ታክሲንም አስቡት፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጉዞዎች የጉዞው ተመን መንግሥት ከሚተምነው በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ውል በተዋዋዮች መካከል በፈቃድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሁለቱም ፈቅደው ያደረጉት ስለሆነ ነው፡፡

በሠላም አውቶቡስና በስካይ አውቶቡስ የሚደረጉት የመጓጓዝ ውሎች በሁለቱ ወገኖች ነጻ ፈቃድ የሚደረግ ውል በመሆኑ በመንግሥት ከተተመነው ተመን በላይ መስማማት የሚቻል ስለመሆኑ ሌላ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በእነዚህ አውቶቡሶች የሚደረግ የመጓጓዝ ውል በዋጋ ደረጃ ከመደበኛ አውቶቡሶች የበለጠ ነው፡፡ ውል ስለሆነ ሁለቱም ወገኖች እስከተስማሙ ድረስ የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ በነዚህ አውቶቡሶች ሌሎች በመንገድ ላይ ስለሚደረጉ የመጓጓዝ ውሎች የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ናቸው፡፡

በሁለቱም ዓይነት ሁኔታ (መንግሥት በተመነው ተመን ወይም ተዋዋዮች በራሳቸው በተስማሙበት ዋጋ) የመጓጓዝ ውል አለ፡፡ በሁለቱም ሁኔታ ምንም ዓይነት መሠረታዊ የውል ልዩነት የለም-ከዋጋ ጉዳይ ውጭ፡፡ በዚህም መሠረት አጓጓዡ ተጓዡን ሰው፣ ጓዙን ወይም ዕቃውን ከታሰበው /በውል ከተገለጸው/ ስፍራ የማድረስ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም የሁለቱም ወገኖች መብትና ግዴታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ነው፡፡ አንድ ሰው መንግሥት በተመነለት ዋጋ ቢዋዋልም ሆነ ከአጓጓዡ ጋር በተለየ ዋጋ ቢዋዋልም ሕግ እና ውል ከሰጠው መብት የሚቀነስበት አግባብ የለም፡፡ ይህንን የተጓዡን መብት እገፋለሁ የሚል ቢኖር አላወቀምና ይወቅ፤ ይህንን አድርጎ ቢሟገትም የገባውን የውል ግዴታ ጥሶ ነውና ይጠንቀቅ፡፡

እንደ ማጠቃለያ፣ አንድ አጓጓዥ መንግሥት በተመነለት መሠረት አገልግሎት ሲሰጥ ውል እንዳለ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በርግጥ ከዚህ ተመን ከፍ ብሎ ወይም ዝቅ ብሎ መስማማት ይቻላል፣ የሚጓጓዘው ሰው እስከተስማማ ድረስ፡፡ የመጓጓዝ ውል ማለት አጓጓዦች (ማለትም የተሽከርካሪ ባለቤቶች) ወይም ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው፣ ማኅበረሰቡም፣ እንደሚያስቡት ከመንግሥት ተመን በላይ መዋዋል ብቻ አለመሆኑን ይወቁ፡፡ ይልቁንም ከተመን በላይ የመጓጓዝ ውል መስማማት እንደ ል ሁኔታ ነው መታየት ያለበት፤ በርግጥም ነው፡፡


[1] የንግድ ሕግ ቁጥር 563፣ 564 እና 565

[2] የንግድ ሕግ ቁጥር 563 እና ከቁጥር 567-603

[3] ከቁጥር 570-576 ያሉትን ይመለከቷል፡፡

[4] የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1675

[5] የንግድ ሕግ ቁጥር 561

[6] ኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ ከመጓጓዝ ውል ተመን በተጨማሪ የነዳጅ ዋጋ በመንግሥት (በንግድ ሚኒስቴር) የሚተመን ነው፡፡ ይህ ሀገሪቱ ከምትከተለው የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር የሚሄድ ነው፡፡ አንዳንድ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ በመንግሥት ሊተመን እንደሚችል አዲሱ የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 685/2002 ይደነግጋል፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 46 ይመለከቷል፡፡ ይህንን ለመረዳት በቅርቡ መንግሥት የስኳር፣ የዘይት፣ የሥጋ፣ እንዲሁም የአንዳንድ የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ ተመን አውጥቶ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፤ እስከ አሁንም አለ፡፡

[7] የንግድ ሕግ መጽሐፍ 2፣ ምዕራፍ 2፣ ክፍል 1፣ አንቀጽ 567

[8] ነገር ግን በአውሮፕላን የሚደረግ የመጓጓዝ ውል የሆነ እንደሆነ ለተጓዡ ትኬት መቁረጥ ግዴታ ነው፤ የንግድ ሕግ ቁጥር 606(1)፡፡ ትኬት መቁረጥ ውል ለመመሥረት የሚያስፈልግ ቅድመ ሁኔታ ነው-በአውሮፕላን ለሚደረግ የመጓጓዝ ውል፡፡

[9] የንግድ ሕግ ቁጥር 567(1)

[10] የንግድ ሕግ መጽሐፍ 2፣ ምዕራፍ 2፣ ክፍል 1፣ አንቀጽ 568-569

[11] በጓዝ ትኬት ላይ ሊሰፍሩ ስለሚችሉ ዝርዝር ሁኔታዎች በቁጥር 568 ሥር ተቀምጧል፡፡ በአውሮፕላን ላይ የሚደረግ የመጓጓዝ ውል ሲሆን ደግሞ የጓዝ ትኬት መስጠት ግዴታ ነው፡፡ የንግድ ሕጉን ቁጥር 608 ይመለከቷል፡፡

[12] ከመንገደኛ ትኬት ጀርባ የሚጻፉ ነገሮች የውሉ አካሎች ናቸው፡፡ ‹‹የመንገደኛ ትኬት ቢጠፋ (ሁለት) እጥፍ ያስከፍላል›› እና ሌላም የሚሉ ጽሑፎች ሁለቱም ወገኖች የሚገዙባቸው የመጓጓዝ ውሉ ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህም በንግድ ሕጉ ቁጥር 567(2) ሥር ሊካተቱ እንደሚችሉ ሕጉ በግልጽ ይናገራል፡፡

[13] ነገር ግን በተለምዶ አንድ ተጓዥ በእጁ የሚይዛቸው ወይም ሊይዛቸው የሚችሉ ጓዞች ዋጋ አይከፈልባቸውም፡፡

[14] እንዲያውም ይህ ነገር የመጓጓዝ ውል ልዩ ሁኔታ (Exception) ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው መርህ ግን መንግሥት በሚተምነው መሠረት መዋዋል ነው፡፡

Advertisements

One thought on “ስለ መጓጓዝ ውል (Contract of Carriage)

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s