ስለ መገበያያ ገንዘቦቻችን፣

ስለ መገበያያ ገንዘቦቻችን፣

እኔ የምላችሁ ሰዎች፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቦች (ብር) ተለጥፈው፣ ለምሳሌ መስታወት ላይ፣ አይታችሁ ታውቃላችሁ? እኔ ብዙ ጊዜ ገጥሞኛል፤ ለምሳሌ ፀጉር ቤቶች እና ፎቶ ቤቶች፡፡ የሚገርመው እኔ ያየሁዋቸው እነዚህ ቤቶች ከአንድ ብር አንስቶ እስከ መቶ ብር ድረስ ያሉትን ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘቦች ለጥፈው አስተውያለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሰዎች ፎቶ አልበማቸው ውስጥ ሥራ ላይ ያለ ሕጋዊ ገንዘብን ሲያስቀምጡ አያለሁ፡፡ እኔ በነዚህ ቦታዎች አስተዋልኩ እንጅ በሌሎች ቦታዎችም ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ይህ ድርጊት ግን አግባብ ነው ወይ፣ ተጠያቂነትስ አያስከትልም ወይ ብዬ ራሴን የጠየኩት ግን በቅርቡ ነው፡፡
የሚለጠፉት ወይም የሚቀመጡት ገንዘቦች የውጭ አገር ገንዘቦች፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገንዘቦች እና አሁን በሥራ ላይ ያሉ ሕጋዊ ገንዘቦች ናቸው፡፡ የቀድሞዎቹ ገንዘቦች ሥራ ስለሌላቸው (የግለሰብ) ሙዚየም ውስጥ እንደተቀመጡ እንቁጠረው፡፡ የውጭ አገር ገንዘቦች እና በሥራ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ገንዘቦች፣ በሥራ ላይ እስካሉ ድረስ መስታወት ውስጥ መለጠፋቸው ግን አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ (የውጭዎቹ፣ ውድ አገራችን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እያስጨነቃት፣ መስታወት ውስጥ መለጠፍ ምን ይሉታል? ምን ያህል ሆኖ ነው እንዳትሉኝ፤ ምንም ያህል ትንሽ ገንዘብ ይሁን!)
ሥራ ላይ ያለን ሕጋዊ ገንዘብ በመስታወት ውስጥ መለጠፍ ዘርፈ-ብዙ አሉታዊ ውጤቶች አሉት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ገንዘቡ ምንም እንኳ የአምጪው (ገንዘቡን በእጁ የያዘው ሰው) ቢሆንም፣ ንብረትነቱ ግን የመንግሥት/የሕዝብ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ላንሳ፤ ገንዘብ የተሰራው ለመገበያያ፣ ሰው ሰርቶ፣ አትርፎ፣ እንዲገለገልበት፣ ሌላ ሰውም እንዲገለገልበት ነው፡፡ ገንዘብን በሚሰራበት ጊዜ ገንዘቡ ስለሚዘዋወር ሁሉም ሰው የገንዘቡ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የገንዘቡ ባለቤት መንግሥት ነው የምለው፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ሰው ገንዘብ ኖሮት ካልተጠቀመበት፣ ይልቁንም ቀብሮ ካስቀመጠው፣ ከፍተኛ ጉዳት ከሚደርስበት አካል መካከል አንዱ መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት መጎዳት ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ደግሞ (ጭቁኑን) ሕዝብ ነው፡፡ የቀድሞ ሰዎች ገንዘባቸውን በማድጋ ወይም ማሰሮ ወይም እንስራ አድርገው መሬት ቆፍረው ይቀብሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ሲሞቱ እንኳ ለወራሾቻቸው ሳይናገሩ እየቀሩ ገንዘቡ እንዲሁ የምድር ቀለብ ሆኖ ለብዙ ዘመን ይኖራል፡፡ በአጋጣሚ የተገኘም እንደሆነ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ እንዲያውም ብርን መሬት ውስጥ የመቅበሩን ነገር ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው ውስጥ ክፉኛ ኮንነውታል፤ ሕዝቡም ብርን መሬት ውስጥ ከመቅበር ይልቅ ቢሰሩበት ብዙ ነገር ሊያተርፉበት እንደሚችሉ በዚሁ መጽሐፋቸው አስገንዝበዋል፡፡ (ሰፋ ላለ ሐተታና ትንታኔ መጽሐፉን ያንብቡ፡፡) ዛሬ ላይ የምናየው ገንዘብን መስታወት ውስጥ መለጠፍም ሆነ አልበም ውስጥ መወሸቅ ገንዘብን ከመቅበር ጋር የሚተካከል የአላዋቂነት ሥራ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ገንዘብን መስታወት ውስጥ መለጠፍ ጉዳቱ ገንዘቡ ቢሰራበት ወይም ባንክ ውስጥ ቢቀመጥ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም/ትርፍ ስለሚያስቀር ነው፡፡ ገንዘብ ቢሰራበት ያተርፋል፡፡ ባንክ ውስጥ ቢቀመጥ፣ ለአስቀማጩ ወለድ ያስገኛል፤ ለተበዳሪው ሰርቶ ያተርፍበታል፤ ባንኩ አበድሮ ወለድ ያገኝበታል፡፡ ስለዚህ ሦስትና ከዚያም በላይ የሆነ ጉዳት ነው የሚያስከትልብን፡፡
ገንዘቡ ቢበላሽ እንኳ ጉዳቱ ለጊዜው ለአምጭው ቢመስልም በቀጣይ ግን መንግሥትና ሕዝብ መጎዳታቸው የማይቀር ነው፡፡ስለዚህ ባንኮች ስለ ገንዘብ አያያዝ የሚያስተምሩትን ከልብ መቀበል ብዙ ጉዳት ያስቀርልናል፡፡ ገንዘብም ቢሆን አስፈላጊ ለሆነ ወጭ ኪሳችን ውስጥ ከያዝን፣ ቀሪው ባንክ ውስጥ ቢቀመጥ ነው የሚጠቅመን፡፡
ይሕስ ሆነና በሥራ ላይ ያለን ሕጋዊ ገንዘብን በመሥታወት፣ በአልበም ሆነ በሌሎች ነገሮች ውስጥ ማስቀመጥም ሆነ ገንዘብ እንዲበላሽ ማድረግ ያለው ሕጋዊ ውጤት ምንድን ነው የሚለውን ልናገር፡፡ (ወዮ! ይቺን ጉዳይ ሕግ ጠባቂው ከሰማ ብዙ ሰዎች መታሰራቸው ነው፤ ደግሞ አላወቅሁም ማለት አይሠራ፤ የንጉሥ ሐሙራቢ “ሕግን አለማወቅ ከቅጣት አያድንም::” የምትለው ሕግ እኮ እስከ አሁን ድረስ የዘለቀች ታላቅ የወንጀል ሆነ የፍትሐ ብሔር ሕግ መርህ ናት፡፡) ለማንኛውም የወንጀል ሕጉን እንመልከተው፡፡
አዲሱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ ከላይ የጠቀስኩትን ዓይነት ድርጊት፣ በተለይም ገንዘቡን እየለጣጠፉ ማበላሸት፣ ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ሥር ይመድበዋል፡፡ በዚህም መሠረት አንቀጽ 358 ዋጋን ዝቅ ማድረግ (Debasing) በማለት “ማንም ሰው በኢትዮጵያ ወይም በውጭ አገር ሙሉ ዋጋውን እንደያዘ መገበያያ እንዲሆኑ በማሰብ በሜካኒካል፣ በፊዚካል፣ ወይም በኬሚካል ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ ተጠቅሞ ሕጋዊ የሆኑትን ገንዘቦች ዋጋቸው ዝቅ እንዲል ያደረገ እንደሆነ፤ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል::”

ስለዚህ እንዲህ አይነት ድርጊት አንደኛ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል፤ ዳግመኛም ወንጀል መሆኑን አውቀን ከድርጊቱ እንቆጠብ፤ በመጨረሻም ለሌሎች እናስተምር፡፡

ቸር እንሰንብት!

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s