ዳኒ የሕይወት ስንቅ፤

 

ዛሬ ይህን ጉዳይ ሳልጽፈው ብቀር፣ ቃልን መብላት ስለሆነ ኅሊናዬ ምን ያህል እንደሚወቅሰኝ አውቀዋለሁ፤ የመማር ትርጉሙም ይጠፋብኛል፡፡ ለዚህም ነው ሃሳብንና ድርጊትን አዋህጄ ይቺን ጽሁፍ ለመጻፍ የተበረታታሁት፡፡ ለመጻፍ ያስገደደኝ ጉዳይ ዕለተ ቅዳሜ ነሐሴ 18፣ 2005 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ሻሸመኔ ከተማ የርቀት ትምህርት ለማስተማር ለመጓዝ በተሳፈርኩበት መኪና ውስጥ ያጋጠመኝ ነገር ነው፤ መጥፎ ድርጊት ሳይሆን እጅግ ደግ ነገር ነው፡፡

ወጣት ነው፤ ሰላሳ ዓመት አካባቢ ይሆነዋል፡፡ ዳንኤል ግርማ ገብረ እግዚአብሔር ይባላል፤ በቅጽል ስሙ “ዳኒ የሕይወት ስንቅ” ይባላል፡፡ እሱ ከኛ ጋር የተሳፈረው ግን እንደሌሎቻችን የግል ጉዳይ ኖሮት ሳይሆን ተሳፋሪውን/ተጓዡን ለማስተማር ነው፡፡ መልኩ ቀይ ሁኖ መካከለኛ ቁመት አለው፤ ጢሙ አጠር ቢልም አብዛኛውን የፊቱን ክፍል ሸፍኖታል፤ ጥርሶቹ የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ሰዎችን ጥርስ መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ አይጠይቅም፤ ጥርሶቹን በንግግርም ሆነ በሳቅ ፈልቀቅ ሲያደርጋቸው እስከ መጨረሻው የመንጋጋ ጥርሶቹ ድረስ ቀለማቸው አንድ ነው፡፡ ወደ ዋናው ሥራው ሲሰማራ ባለ ጥቁር ቀለም ፍሬም መነፅሩን ይሰካል፡፡ ሐኪሞች የሚለብሱትን ነጭ በርኖስ ይለብሳል፤ አፉን ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓርማ ባለበት ቀይ ማፈኛ/Mask/ ይሸፍናል፤ ንግግር ሲያደርግ የማንንም ሰው ስሜት መግዛት ይችላል፡፡ አንደበቱ የረታ ነው፡፡ የዳኒ ትልቁ ስብእናው ግን አፍአዊ ገጽታው ሳይሆን ከውስጡ የሚመነጨው ነጸብራቅ ነው፡፡ ውስጡ ብርሃን ፈንጣቂ ነው፡፡

ዳኒ ሥራውን የጀመረው ገና ከቃሊቲ መናኸሪያ ስንወጣ ነው፡፡ “እባካችሁ ተሳፋሪዎች የመኪናውን ሁሉንም መስኮቶች ክፈቱ” በማለት ነው ማስተማሩን የጀመረው፡፡ ዳኒ የሕይወት ስንቅ የሚያስተምረው የቲቢ በሽታን ለመከላከል ተሳፋሪዎች በጉዞ ወቅት የመኪና መስኮቶችን መክፈት አለባችሁ እያለ ነው፡፡ ይህን ትምህርት የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙኀን ሲያስተምር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ዳኒ ይህንን ትምህርት ነው በስፋትና በቁርጠኝነት በአካል ከተሳፋሪዎች ጋር በመገኘት ነው ትምህርቱን ለማስተማር በቁርጠኝነት እዚያ መኪና ውስጥ የተገኘው! በኋላ እንደተረዳሁት ግን ይህንን በመኪና ውስጥ የማስተማሩን ነገር ከአስር ዓመት በላይ እንደሠራ ነው፡፡

ዳኒ ነዋሪነቱ ሀዋሳ፣ በሙያው ደግሞ ጋዜጠኛና ደራሲ ሲሆን በኤፍ. ኤም አዲስ 97.1 ላይ እንደሚሠራ ራሱን ሲያስተዋውቅ ነግሮናል፡፡ “የብርሃን ናፍቆት” የሚል መጽሐፍ የጻፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ አንድ መጽሐፍ ለማሳተም ማተሚያ ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት የሜዲካል ነርስ እና ሳይኮሎጅ ተምሯል፡፡ ይህንን መኪና ውስጥ የማስተማሩን ሥራ የሚሰራው ግን በበጎ ፈቃደኝነት ነው፡፡ ዳኒ፣ ነፍሱን ይማረውና የኮሜዲያን አለባቸው ተካ የሥራ ውጤት ነው፡፡ አለባቸው ተካ ካስተማራቸው ጎዳናዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ እርሱም የአለባቸውን ፈለግ በመከተል ነው በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማራው፡፡ አልፎ ተርፎም አለባቸው እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በተራው የሚያሳድጋቸው በርካታ ጎዳናዎች እንዳሉት ተናግሯል፡፡

በጉዞ ላይ እንዳለን፣ ዳኒ የመኪና መስኮቱን ክፈቱ ሲል ከተሳፋሪው ጋር አንዳንድ እሰጣ-ገባ ገጥሞት ነበር፡፡ ሁሉንም ግን በትእግስትና እውቀት በተሞላበት መንገድ በማስረዳት ሊረታ ችሏል፡፡ የሚያነብ ንባቡን ትቶ፣ የሚተኛ እንቅልፉን አቋርጦ፣ በጆሮ ማዳመጫ የሚያዳምጥ ማዳመጫውን ነቅሎ፣ በሃሳብ የነጎደውም ሃሳቡን ገትቶ፣… ጆሮውንና ኅሊናውን ዳኒ ላይ ተከለ፡፡ ስለ ቲቢ በሽታ መተላለፊያ መንገድ እና ስለሚደረግ ጥንቃቄ ለ75 ደቂቃ ያህል ትምህርት እንደሚሰጥ ከገለጸ በኋላ ብእርና ወረቀት ላልያዙት የራሱን በመስጠት ማስተማሩን ተያያዘው፡፡ ከዚያማ እኛ ተጓዦቹ ወንበራችን ላይ ዘና ብለን ተቀምጠን ዳኒ ደግሞ በሚወዛወዝ መኪና ላይ እየተወዛወዘ፣ ክፍ ዝቅ እያለ፣ ወገቡ እየተቀጨ፣ በሚጮህ መኪና ውስጥ ሆኖ ለ49 ሰው እንዲሰማ ላንቃው ተከፍቶ እንደ ቁራ እየለፈለፈ፣ ምራቁ እየደረቀ፣ በሃይል እየተነፈሰ፣ የሰው ፊት እንደ እሳት እየገረፈው፣ … ያስተምራል፡፡ ዶት ቲቢ እና MDR ቲቢ (መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ማለት ነው) ስለሚባሉ የቲቢ ዓይነቶች በስፋት አስተማረ፡፡ በተለይ MDR ቲቢ በጣም አደገኛና በህክምና ላይ ያሉ ሙያተኞችንም በተለይ እያጠቃ እንደሆነ ተናገረ፡፡ የመኪና መስኮትን በመክፈት 85% ቲቢ አስተላላፊ ባክቴሪያን መከላከል እንደሚቻል፣ ስናነጥስ እና ስንስል ደግሞ አፋችን በእጃችን ከማፈን ይልቅ በክንዳችን ብናፍን እንደሚመረጥ ተናግሯል፡፡ በምናነጥስበት ጊዜ ከ4500-1.5ሚሊዮን፣ በምንስልበት ጊዜ ከ3500 እስከ 1ሚሊዮን፣ በንግግር፣ በማዛጋት፣ እና በሌሎች ጊዜ ደግሞ ከ200-1000 የሚሆኑ ቲቢ አስተላላፊ ባክቴሪያዎች ከአፋችን እንደሚወጡ፤ አንድ ጊዜ አየር ላይ የተረጨ ባክቴሪያ ደግሞ ከ5-8 ቀን አየር ላይ እንደሚዉል አስረድቷል፡፡ ለዚህም ነው የመኪና መስኮት መከፈት አለበት የሚባለው፤ ምክንያቱም መስኮት ከተከፈተ፣ መኪና ውስጥ የሚቆይ ባክቴሪያ አይኖርም፣ ከ5-8 ቀን የሚቆይበት አጋጣሚ አይፈጠርም፡፡ ደግሞስ ወበቁ፣ ላቡ፣ ሽታ ምናምን የሚባሉ የጉዞ አስቀያሚ ነገሮችስ መስኮት ከተከፈተ ድራሻቸው እኮ ነው የሚጠፋው፡፡

ዳኒ ትምህርቱን ሲሰጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከቁራን እያጠቀሰ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ለምናመልከው አምላክ ታማኝ እንሁን በማለት ትምህርቱን ቀጥሏል፡፡

ዳኒ ምንም እንኳ ለ75 ደቂቃ የሚደርስ ትምህርት ነው ይበል እንጅ ሻሸመኔ እስክንደርስ ድረስ ማስተማሩን አላቆመም፤ አልፎ አልፎ እረፍት ከማድረጉ በቀር፡፡ ከቃሊቲ ስንነሳ መስኮት ቢከፈት እንታመማለን ሲል የነበረው ሁሉ ሻሸመኔ ስንደርስ፣ ዳኒ እንዴት ነው አሁንስ ታመማችሁ ብሎ ሲጠይቅ አንዳች ታመምኩ ያለ አልነበረም፤ ሁሉም በጤና ነው የደረሰው፤ እንዲያውም ይግረማችሁና ሁሉም የመኪና መስኮት የተከፈተ እንኳ አይመስልም ነበር፡፡ እንዴት አይነት ግሩም ነገር ነው እባካችሁ!! እኔ ራሴ እሰከ አሁን በተጓዝኩባቸው ረጃጅምም ሆነ አጫጭር ጉዞዎች እንደዚያ ቀን ተመችቶኝ አያውቅም፤ የዘመኔ ሁሉ ምርጥ ጉዞ ነበር፡፡ የኔ ብቻ ሳይሆን የዚያ መኪና ተሳፋሪዎችም ምርጥ ጉዟቸው እንደሆነ አልጠራጠርም!

ወደ ዋናው ጉዳይ ልመልሳችሁ፡፡ ዳኒ የሕይወት ስንቅ ቀደም ባሉት ጊዜያት ስለ ፍቅር፣ ስለ ትዳር፣ ስለ ኤች. አይ. ቪ ቫይረስ በመኪና ጉዞ ላይ ያስተምር ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሪፖርተር ጋዜጣ በሰኔ 16፣ 2002 ዓ.ም ዕትሙ “ወጣት” ዐምድ ስር ስለ ዳኒ ሥራ እና የሕይወት ጉዞ አስነብቦ ነበር፡፡ የጋዜጣውን ጽሑፍ ራሱ ዳኒ ለሁሉም ተጓዥ አባዝቶ ሰጥቶን አንብበነዋል፡፡ ቤተሰቦቹን በኤች. አይ. ቪ ሳቢያ ገና በስምንት ዓመቱ በማጠቱ፣ ከአያቶቹ ጋር ቢኖርም ዳሩ ግን ‘ገፊ’ እየተባለ መኖር ስለሰለቸው ለጎዳና ሕይወት ተጋልጥዋል፡፡ ከዚያም አቦምሳ ከተማ ከአንድ ሻይ ቤት በ40 ብር ተቀጥሮ ቢሰራም እንኳ አሰሪው ጉልበቱን ከመበዝበዝ ውጭ ደመወዙን ሊሰጠው ባለመቻሉ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ለጎዳና ሕይወት ተዳርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ 10 ዓመት በጎዳና ሕይወት አሳልፏል፡፡ በዚህን ጊዜ ነው አለባቸው ተካ አግኝቶት በሱ ጥላ ስር ያረፈው፡፡ ስለ አለባቸው ተካ ተናግሮ አይሰለቸውም፤ እንደርሱ ባይሆንም እንኳ ፈለጉን ለመከተል ሌት ተቀን እንደሚሠራ ይናገራል-ዳኒ፡፡

ዳኒ እኛን ባስታመረባት በዚያች ቀን ስለ ቲቢ ብቻ አይደለም ያስተማረው፡፡ ስለ ማንበብ ብዙ ተናግሯል፤ አንብቡ፣ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል በማለት ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ ስለ ህጻናት ጉልበት ብዝበዛ አስተምሯል፡፡ “የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ በኔ ይቁም!” ሲል ውስጡን ሳግ እንደሚያንቀው ከፊቱ በግልጽ ይነበባል፡፡ ስለ ልመና መጥፎነት አስተምሯል፡፡ ዳኒ እንዲህ ይላል፤ ትልቅም ሆነ ሕጻን ልጅ ሲለምኗችሁ በምንም ዐይነት ሁኔታ ሳንቲም ሆነ ብር አትስጡ ይላል፤ ምክንያቱም ሳንቲም ስትሰጡ ከዚያ ሕይወት መውጣት ያቅታቸውና ለማኝ ሆነው ይቀራሉ፡፡ የሚበላ ነገር ብቻ ስጡ፤ አምስት ሳንቲም ከምትሰጡ፣ የመቶ ብር ምግብ ገዝታችሁ ብትሰጡ ይሻላል ይላል፡፡ ልመናን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ዳኒ ጥሩ መፍትሔ ያቀረበ ይመስለኛል፡፡ ስለ ጎዳና ሕይወት መራርነት ይናገራል-ዳኒ፡፡ የጎዳና ነዋሪዎች ለሱስ የተጋለጡ ናቸው፤ ወደውት ሳይሆን ተገደው፡፡ እሱ ራሱ 18 ዓመት ሲጋራ እንዳጨሰ፣ አሁን ግን እንደተወ ይናገራል፡፡ ዳኒ ስለ ጎዳናዎች ሲናገር ሳግ ይተናነቀዋል፡፡ ለጎዳና ነዋሪዎች ፍቅር ስጡ ይላል፤ እነርሱ እኮ የኛው ሰዎች ናቸው፤ ደግሞም ይላል ዳኒ፣ ሁላችንም ቢሆን ከልብሳችን ሥር እኩል ነን፣ የሚለየን ልብሳችን ነው፤ ጎዳናዎች ኅሊናቸው ንጹሕ ነው፡፡ ከታመኑ እንደእነሱ ታማኝ የለም፤ ከተጠሉ ደግሞ እንደነሱ አደገኛ የለም፡፡ ሌሊት መንገድ ላይ ብትወድቅ፣ አደጋ ቢደርስብህ፣ ሱስ ያለበት ሰክሮ ቢወድቅ…ቀድመው የሚደርሱልህ፣ ቤትህ የሚያደርሱህ፣ ፖሊስ የሚጠሩልህ፣ የሚጠብቁህ እነርሱ ናቸው፡፡ ደግሞስ አለ ዳኒ፣ በአብዛኛው የጎዳናዎች ምግብ ቡሌ ነው፤ ቡሌ መብላት ያሳፍራል እንዴ? ምግብ መብላት ያሳፍራልን? ነፍሰ-ጡር ሴት ቡሌ አማረኝ ብላ ከሆቴል ተገዝቶ ይቀርብላት የለም እንዴ? ዳኒ ከጎዳና ሕይወት ወጥቶ፣ አሁንም እንኳ በሳምንት 2 ጊዜ ከሆቴል ቡሌ ገዝቶ እንደሚበላ ነግሮናል፡፡

ቡሌን በተመለከተ አንድ ነገር ለሁላችንም በጥብቅ አደራ ብሎናል፡፡ እነሆ እኔም መልእክቱንና አደራውን ለሌሎች ላስተላልፍለት! “ሆቴል ወይም ማንኛውም ምግብ ቤት ምግብ በልታችሁ እጃችሁንና አፋችሁን በሶፍት ወረቀት ከጠረጋችሁ በኋላ ሶፍቱን ትሪው ላይ አትጣሉት፣ አስተናጋጁ ሶፍቱን ከትራፊው ምግብ ላይ ስለሚደባልቀው ቡሌው ይበላሻል፡፡ ይልቁንም የጠረጋችሁበትን ሶፍት ወረቀት መሬት ላይ ጣሉት፣ ያኔ ተጠርጎ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ይጣላል፡፡” ሶፍት ትሪ ላይ በሚጥሉ ሰዎች ሳቢያ ዛሬም ድረስ ቡሌ ሲበላ ሶፍት እየለቀመ እንደሆነ አምርሮ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ይህችን ነገር ሁላችንም አደራ!!! አደራ!!! አደራ!!!

ዳኒ እስከ ሻሸመኔ አብሮን የሕይወት ስንቅ እየሰጠን ሲሄድ ድርቅ ያለ ትምህርት እያስተማረ ብቻ አይደለም፤ እያዝናናም ነው-ድሮውንስ የአለባቸው ሆኖ!!! ዳኒ ኮሜዲነትም ይወጣዋል፡፡ ትምህርቱን አስተምሮ ከጨረሰ በኋላ አንድ የስልክ ጥያቄ፣ አንድ ስለ ቲቢ ካስተማረው እና አንድ ደግሞ የማንበብን ነገር ለማጎልበት፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ ስለእርሱ ከተጻፈው አንብበን አንድ ጥያቄ፣ በአጠቃላይ ሦስት ጥያቄ ነበር-ለዚያውም ሽልማት ያለው!! ሽልማቱስ ሽልማት መሰላችሁ፤ ለአዲስ ዓመት መዋያ የሚሆን ብር በቼክ ሊያሳፍሰን! ሽልማቱ ተዘጋጅቶ የነበረው ዝዋይ ከተማ ስለነበር፣ ዝዋይ ላይ መኪናው ለአፍታ ቆሞ ለሽልማት የተዘጋጀውን ስናየው በሽልማት መጠቅለያው ላይ አበጥ አበጥ ብሎ ስናየው ለማዝናናት ብሎ እንደሆነ ገባን፡፡ ሽልማቱ ለጥያቄው መላሾች ለመስጠት ሽልማቱን የሚሰጡ ሰዎች ከተጓዦች መካከል በዕድሜ ጠና ያሉት ተመርጠው ሽልማቱን ሰጡ፡፡ ሦስቱም ሽልማቶች ሲከፈቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በፍሬም ተደርገው ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ ቅልጥ ያለ ጭብጨባ መኪናውን ያደምቀዋል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ሲቀልጥ የፎቶ ካሜራ ይዤ ቢሆን ኖሮ በፎቶ አስቀረው ነበር፤ ታዲያ ሳይቸግረኝ ዘነጋሁት፡፡ ግድ የለም፣ እንዳይጠፋ አድርጌ በኅሊናዬ ስየዋለሁ፡፡ ውድ አንባቢያንም በኅሊናችሁ እንደምትስሉት እገምታለሁ፡፡

አይይይይ….ልዘነጋው ነበር፡፡ ደግሞ ጨረታውስ! ዳኒ በሀዋሳ በሚያሳድጋቸው ጎዳናዎች እጅ የተሠሩ ውብ የኪስ ቦርሳዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር፡፡ አንዷ በ30 ብር መነሻነት አንድ የግንባታ ሙያ ያለው ተጓዥ በ350 ብር አሸንፎ ወሰዳት፡፡ አንዷን ደግሞ አንድ ሰውዬ በ200 ምናምን ብር አሸንፎ ከወሰዳት በኋላ እንደገና መልሶ በጨረታ እንድትሸጥ አቅርቧታል፡፡ ይህ ሁሉ ማሽር የሚቀልጠው እኮ መኪናው፣ ለጥ ብሎ በተዘረጋው የአዲስ አበባ-ሀዋሳ መንገድ፣ መኪናው እየተወነጨፈ ነው፡፡ መኪናችን ዝዋይ ከተማ እሽግ ሽልማቶችን ለመቀበል ለአፍታ ያህል ከመቆሙ በቀር አንድም ጊዜ አልቆመም ነበር፡፡ (በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ባደረኳቸው ጉዞዎች እሰጣ-ገባ ገጥሞኝ ስለነበር፣ የትራንሰፖርት መኪናዎችን ነገር ከሕግ አኳያ ሌላ ጊዜ፣ ጊዜ ገዝትን  አጫዉታችዋለሁ፡፡)

በመጨረሻ አንድ ነገር ልናገር፡፡ ዳኒ ለአዲሱ ዓመት መቀበያ የሚሆን ሀዋሳ ለሚገኙ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጎዳናዎች የምግብና የልብስ ዕደላ መርሐ ግብር ለማድረግ ዐቅዶ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህንን ሃሳቡን ለተሳፋሪው ሲናገር፣ ሁሉም ሰው በሚችለው መጠን ይህን ሃሳቡን ለማገዝ ወደ ኋላ ያለ የለም፤ ምላሹን ወዲያውኑ ነበር የተቀበለው፡፡ አንዲት እናት 50 እንጀራ ለመሥጠት፣ አንድ ጎልማሳ የሁለት ኪሎ ሥጋ ዋጋ እዚያው ላይ ሠጥቷል፤ አብዛኛዎቻችን እኔንም ጨምሮ ደግሞ ልብስ እና ሌላ ነገር ለማበርከት በተዘጋጀልን ቅጽ ከነአድራሻችን ሞልተናል፡፡ በሀዋሳና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሆነው መርዳት ለሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለመቀበል የተመደቡ ሰዎች አሉ፡፡ ዳኒ በሁሉም ቦታ ተወካይ እንዳለው በኩራት ተናግሯል፡፡ ቃል የተገባውን በስልክ እየደወሉ ለመጥራት የካርድ ገንዘብ ያስፈልግ ስለነበር ከመካከላችን አንዱ ተሳፋሪ ለካርድ የሚሆን ገንዘብ ለግሷል፡፡

እንግዲህ ልሰናበታችሁ፡፡ ይህንን ለምታነቡ ሰዎች በሙሉ፣ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱትን ነገሮች ሁሉ ለሌሎች በመናገርም ሆነ በማስተማር እንድትተባበሩ ዳኒ ለኛ በሰጠን አደራ መሠረት እኔም አደራ እላችዋለሁ!!! ከዚህ በላይ ባለው አንቀጽ ለተጠቀሰው ዓላማ እርዳታ ማድረግ ብትሹ ደግሞ የዳኒ ስልክ ቁጥር 0925606300 ወይም 0921810630 ስለሆነ ተጠቀሙ፡፡ ታዲያ Miscall አይደረግም፡፡

ደግ ሰው አያሳጣን፡፡ ለትእግስታችሁ የትእግስት አምላክ ትእግስት ይጨምርላችሁ!

በሉ ደህና ሰንብቱልኝ፡፡

 

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s