የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ በተረቀቀው መመሪያ ላይ የተሰጠ አስተያየት፤

በላይነው አሻግሬ

ክፍል 1

  1. 1.    መግቢያ፣

ሰሞኑን እያነጋገሩ ካሉት አገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ያዘጋጀው የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ረቂቅ መመሪያ (Draft Directive) ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በረቂቅ መመሪያው ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ለተለያዩ መንግስታዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ተቋማት አቅርቧል፤ እነዚህ አካላትም አስተያየታቸውን እየሰጡበት ነው፡፡ አስተያየት የሚሰጡት አካላት ረቂቅ መመሪያውን ከተለያየ አቅጣጫ በተለይም ከሕገ-መንግሥት፣ ከሃይማኖት ነፃነት፣ (ከመንግሥት) ጣልቃ ገብነት እና ከሌሎችም ጉዳዮች አንጻር እየተቹት ይገኛሉ፡፡ እኔም ጉዳዩን ከሰማሁበት ቀን አንስቶ፣ ረቂቅ መመሪያውን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ብዙም ሳልደክም ተሳክቶልኝ፣ እነሆ ዛሬ ጉዳዩን ከሕግ አንጻር ለመቃኘት አስቤያለሁ፡፡ እንግዲያውስ አብረን እንቆይ!

ወደ ዋናው ጉዳይ ከማምራቴ በፊት እንደ መግቢያ አንዳንድ ነገሮችን ላቅርብ፡፡ አዲሱ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ሥልጣንን የሚወስነው አዋጅ ቁጥር 691/2003 እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ የሃይማኖት ጉዳዮች በተለይም ምዝገባንና ሌሎች ተያያዢ ጉዳዮችን የሚመለከተው አካል የፍትሕ ሚኒስቴር ነበር፡፡ ከ2003ዓ.ም ወዲህ ጉዳዩ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር (ፌ.ጉ.ሚ) ተሰጥቶታል፡፡ አሁን ፌ.ጉ.ሚ ያረቀቀው የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2005 ዓ.ም የመጀመሪያው ነው፡፡ በሕግ ተዋረድ (Hierarchy of Laws)[1] መርሕ መሠረት በተያዘው ጉዳይ ላይ መመሪያ ማውጣት የሚችለው ይኼው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነው፡፡  አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ግን ሃይማኖትን ያክል ትልቅ ጉዳይ በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ ያውም ፌ.ጉ.ሚ፣ በመመሪያ መልክ መውጣት አይገባውም እያሉ ነው፡፡ ረቂቅ መመሪያው በሰባት ልዩ ልዩ ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን ክፍል 1 ጠቅላላ፣ ክፍል 2 ምሥረታ፣ ምዝገባና፣ ስያሜና የዓርማ አጠቃቅም፣ ክፍል 3 የውጭ ዜጎችን ስለማሰራት፣ ክፍል 4 የሃይማኖት ተቋማት መብት፣ ግዴታና ስለተከለከሉ ነገሮች፣ ክፍል 5 ሪፖርት፣ ዕድሳት፣ ክትትል እና ህጋዊ ሰውነትን ስለማጣት፣ ክፍል 6 ስለ አገልግሎት ክፍያ፣ አለመግባባቶችን ስለመፍታትና ስለ ቅሬት አቀራረብ፣ እና የመጨረሻው ክፍል 7 ደግሞ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ይህንኑ ረቂቅ መመሪያ በተመለከተ ላነሳቸው ያሰብኳቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡

  1. 2.   የረቂቅ መመሪያው መግቢያ/መቅድም፣

ከረቂቅ መመሪያው መግቢያ/መቅድም ልጀምር፡፡ የአንድ ሕግ መቅድም ስለ ሕጉ አጠቃላይ ዓላማ ከሚያስረዳን የሕጉ ክፍል በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ የሕግ መቅድም ስለ ሕጉ አስፈላጊነት፣ ከሕጉ በስተጀርባ ስላለው ዓላማ፣ ስለ ወደ ፊቱም የሕጉ ነገር የሚነግረን ስለሆነ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ረቂቅ መመሪያ ሊወጣ የታሰበበት አንደኛው ምክንያት በመግቢያው ሁለተኛ አንቀጽ እንደተጠቀሰው፣ የሃይማኖት ተቋማትን ከመሠረታዊ አሰራር ለውጥ አንጻር ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራትና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ እንግዲህ ረቂቅ መመሪያው መሠረታዊ አሰራር ለውጥ (በእንግሊዝኛው ‹‹Business Process Re-engineering/BPR›› ተብሎ የተጠቀሰውን እንደ መነሻ አድርጎ የተቀረጸ ነው ማለት ነው፡፡ መሠረታዊ አሰራር ለውጥ በሕግ ዓይን ሲታይ እጅግ ብዙ ክፍተቶችን የሚፈጥር ስለሆነ፣ አንዳንድ ጊዜም ሕግ ያስቀመጠውን ነገር የሚገፈትር በመሆኑ፣ ለሕግ መሠረትነት የለውም፡፡ አንድ ሕግ ሊወጣ የሚችለው በተዋረዱ ከዚያ ሕግ በላይ በሆነ ሌላ ሕግ በመመሥረት፣ ወይም ደግሞ አንድ የተቀመጠን ሥርዓት/ፖሊሲ/ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ሕጋዊና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ለማስቀመጥ ነው፡፡ መሠረታዊ አሰራር ለውጥ ስንመለከተው ግን ወይ ሕግ አይደለም፣ ወይም ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ የተቀመጠ አይደለም፡፡ ስለዚሕም መሠረታዊ አሰራር ለውጥን መሠረት አድርጎ ሕግ ማውጣት፣ ይህንን ሕግ ሕጋዊነቱን አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ጥንቱንም የበላይ ሕግ ወይም ፖሊሲን ያልተከተለ ሕግ ማውጣት አይቻልም፡፡ ፌ.ጉ.ሚ ያረቀቀው መመሪያ መሠረታዊ አሰራር ለውጥን መሠረት አድርጎ መነሳቱ፣ ረቂቅ መመሪያውን ተቀባይነቱን ያሳጣዋል፡፡ በርግጥ በረቂቁ ሕግ መግቢያ/መቅድም የመጨረሻ አንቀጽ ላይ፣ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ የመመሪያው መውጣት በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ዋና መነሻ ማድረግ ሲገባው፣ መሆን የሌለበትን መሠረታዊ አሰራር ለውጥን እንደ ቀዳሚ መነሻ ማድረጉ የረቂቅ መመሪያውን ተቀባይነት ውድቅ ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ የረቂቅ መመሪያው ድክመት ገና ከመቅድሙ ጀመረ ማለት ነው፡፡    

  1. 3.  የሕግ ሰውነትን በተመለከተ፣

የሃይማኖት ተቋማት በሕግ የሰውነት መብት ከሚሰጣቸው አካላት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በነገራችን ላይ በሕግ የሰውነት መብት የሚሰጥበትን መንገድ በጠቅላላው በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው አግባብ ባለው ባለሥልጣን ፊት በመመዝገብ ነው፡፡ የግል የንግድ ተቋማት ‹‹በምዝገባ›› የሕግ የሰውነት መብት ከሚሰጣቸው አካላት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም በንግድ ሕጉ ቁጥር 211 እና ከዚያ በኋላ ባሉት የሚገዙ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሕግ የሰውነት መብት ከሚሰጣቸው አካላት መካከል ማኅበራት ይጠቀሳሉ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 404 እና ከዚያ በኋላ ያሉትን ይመለከቷል)፡፡ ማኅበራት ለትርፍ የማይቋቋሙ፣ የህግ ሰውነት ያላቸው ሲሆኑ በርካታ ነገሮችን ያጠቃልላል፤ ለምሳሌ የበጎ አድራጎት፣ ማኅበራዊ-ነክ ተቋማትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ ንግድ ተቋማት ሁሉ ማኅበራትም የሕግ ሰውነት የሚያገኙት አግባብ ባለው ባለሥልጣን ፊት ‹‹በመመዝገብ›› ነው፡፡ ስለነዚህ ማኅበራትም ሆነ የንግድ ተቋማት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አንመለከትም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሕግ የሰውነት የሚሠጠው ደግሞ መንግሥት (የሚኒስቴሮች ም/ቤት) በሚያወጣው ደንብ (Regulation) የሚቋቋሙ እና የሕግ የሰውነት መብት የሚሰጣቸው ናቸው (አዋጅ ቁጥር 25/92 ይመለከቷል)፡፡ ብዙውን ጊዜ በደንብ የሚቋቋሙና የሕግ ሰውነት የሚሰጣቸው የመንግሥት የንግድ ተቋማት ናቸው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ጉዳይ ስንል እነዚህንም አንመለከትም፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሕግ የሰውነት መብት የሚሰጠው/የሚገኘው በሕግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም ሕግ ለአንድ ለነበረ አካል የሕግ ሰውነት መብት አለው ብሎ ሲደነግግ ነው፡፡ ለምሳሌ የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥት፣ የመንግሥት አስተዳደር ክፍሎች (መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት የንግድ ተቋማትን ሳይጨምር) በሕግ የሰውነት መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 እና ከዚያ በኋላ ያሉትን ይመለከቷል፡፡) ከዚህ ላይ አንድ ልናስተውለው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ይኼውም የሕግ ሰውነት ስለተሰጣቸው የሃይማኖት ተቋማት ነው፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት መካከል በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ/ያን (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን) ብቻ ናት፡፡

ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትን በሚመለከት ግን የፍትሐ ብሔር ሕጉ እንደሚናገረው፣ የሚተዳደሩት እነዚህኑ በሚመለከት በሚወጡ ልዩ ሕጎች ነው (ፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 407(1))፡፡ እነርሱን በሚመለከት ልዩ ሕግ ባይኖር፣ እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት እንደ ተራ ማኅበር ተቆጥረው፣ ማኅበራትን በሚገዙት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ይተዳደራሉ (ፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 407(2))፡፡ እንደሚታወቀው የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ እስከ አሁን ድረስ የወጣ ልዩ ሕግ የለም፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበሮችን ለመመዝገብ በ1959 ዓ.ም የወጣው ደንብ ቁጥር 321/59 ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን ውጭ ያሉ የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ እያገለገለ ይገኛል፡፡ እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት ተመዝግበው፣ የሕግ ሰውነት የሚያገኙትና የሚንቀሳቀሱት በዚህ ደንብ መሠረት ነው፡፡ ይህ ደንብ እስከአሁን ድረስ እየተሠራበት ነው፡፡ ስለዚህ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን ውጭ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነት የሚያገኙት እንደ ሌሎች ማኅበራት ሁሉ በምዝገባ ነው፡፡

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የምንመለከተው ስለ ሃይማኖታዊ ተቋማት በተለይ ደግሞ ስለ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ የተጠቀሰውን ረቂቅ መመሪያ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን አንጻር ለመገምገም እሞክራለሁ፡፡

ሃይማኖታዊ ተቋማት በንግድ ሕጉም ሆነ ማኅበራትን በሚገዛው በፍትሐ ብሔሩ ሕግ አይገዙም/አይጠቃለሉም፡፡ ከሃይማኖታዊ ተቋማት መካከል ቀደምትና ጥንታዊ የሆነችው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን የሕግ ሰውነት ያላት ስትሆን ይህንንም በምዝገባ ሳይሆን በሕግ ‹‹እውቅና›› ያገኘችው ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነት ያገኙት በሕግ እውቅና ተሰጥቷቸው ሳይሆን በምዝገባ እንደሆነ ከላይ አይተናል፡፡   

የሕግ ሰውነት መብት የሚሰጠው/የሚገኘው በዋናነት በሦስት መንገድ ሊሆን እንደሚችል ከላይ አይተናል፡፡ የመጀመሪያው ሊቋቋም የተፈለገው አካል በሕግ የሚጠበቅበትን መሥፈርቶች ካሟላ በኋላ አግባብ ባለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ‹‹በመመዝገብ›› ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን የንግድ፣ የበጎ አድራጎት፣ ማኅበራዊ-ነክ፣ እንዲሁም አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማትን ብንመለከት በምዝገባ ተቋቁመው የሰውነት መብት የተሰጣቸው ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሕግ የሰውነት መብት የሚሰጠው መንግሥት በሚያወጣው ‹‹ደንብ›› መሠረት ነው፡፡ በሦስተኛነትም ሕግ አስቀድመው ለነበሩ ተቋማት የሕግ ሰውነት መብት እንዳላቸው ‹‹እውቅና›› ይሰጣቸዋል፡፡

ሕግ እውቅና ሰጣቸው ማለት ምዝገባ አያስፈልጋቸውም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የምዝገባ ዋናው ዓላማው ለሚቋቋመው አካል የሕግ ሰውነት መስጠት ስለሆነ፣ በሕግ እውቅና የተሰጠውን አካል እንደገና ተመዝገብ ማለት በሕግ ዘንድ መሠረት ስለሌለው ነው፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተለያዩ የአስተዳድር አካሎቹም የሕግ ሰውነት እንዳላቸው ሕግ እውቅና ሰጥቷል፡፡ እነዚህ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት፣ የሕግ ሰውነት ለማግኘት እንደገና የሚመዘገቡበት የሕግ ድጋፍም ሆነ መሠረት የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሕግ ሰውነት እያላቸው፣ እንደሌላቸው ሆነው እንዲመዘገቡ የሚገደዱበት የሕግ አግባብ የለም፡፡

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን በ1960ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 መሠረት የሰውነት መብት እንዳለት ሕጉ እውቅና ሰጥቷታል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን ሃገረ ስብከቶች፣ አድባራትና ገዳማት በሕግ እውቅና እንደተሰጣቸው ቁጥር 399 በግልጽ ይናገራል፡፡

እንግዲህ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ሕግ በሚፈቅድለት መልኩ የተቋቋመለትን ዓላማ መሥራት ይችላል፡፡ ለዚህ መብቱ በሕግ የተከለከለ ነገር ከሌለ በቀር ለመሥራት የሚያገደው ነገር የለም፡፡ አንድ ጊዜ የሕግ ሰውነት እውቅና ከተሰጠ ወይም በምዝገባ ከተገኘ፣ ይህ አካል እስካለ ድረስ (እስካልፈረሰ ድረስ) መብቱን ይጠቀማል፡፡ ሌላ ምዝገባም አያስፈልገውም፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት፣ አንድ አካል የሕግ የሰውነት መብት ከተሰጠው በኋላ ሌላ ምዝገባ አያስፈልገውም፡፡ አንድ ጊዜ የተገኘ የሕግ ሰውነት፣ ሁሉንም መብቶች ለመጠቀም ወይም ግዴታዎችን ለመወጣት ስለሚያስችል የሕግ ሰውነት ለማግኘት ድጋሚ ምዝገባ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን በሌላ (አዲስ) ሕግ የተቀመጡ መብቶች ካሉ ሊጠቀም፣ ግዴታዎች ካሉበትም ግዴታዎቹን ሊወጣ ይገባል፡፡

ማኅበራት ቅርንጫፍ ለመክፈት፣ ቤ/ክ/ያን ደግሞ አዲስ ሃገረ-ስብከት፣ ገዳምም ሆነ ደብር ለመመሥረት አዲስ የሕግ ሰውነት ለማግኘት የሚደረግ ምዝገባም የለም፡፡ አንድ ጊዜ የተገኘ የሕግ የሰውነት መብት ለሌላው (በማኅበራት፣ ቅርንጫፍ)፣ በቤ/ክ/ያን ደግሞ ለሀገረ-ስብከት ወይም ለገዳም ወይም ደግሞ ለደብር ያገለግላል፡፡ አንድ ጊዜ የተሰጠ፣ ወይም በምዝገባ የተገኘ የሕግ ሰውነት፣ ይኼው አካል ለሚያደርገው የመስፋፋት ሥራ፣ ሌላ የሕግ ሰውነት ለማግኘት ምዝገባ አያስፈልገውም፡፡ ምናልባት የሚያስፈልግ ነገር/ግዴታ ቢኖር አዲስ በሚመሰረትበት/በሚቋቋምበት አካባቢ ለሚገኝ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማሳወቅ ነው፡፡

  1. 4.  ስለ ምዝገባና ስለመሳሰሉት፣

እስኪ አሁን ደግሞ፣ ረቂቁ መመሪያ በክፍል 2 ሥር ስላስቀመጣቸው የሃይማኖት ተቋማት ምሥረታ፣ ምዝገባ እና ስያሜና ዓርማ/ምልክት አጠቃቀም አንቀጾችን እንመርምረው፡፡

የረቂቅ መመሪያው በክፍል ሁለት የሃይማኖት ተቋም ለመመሥረት ስለሚያስፈልጉ ቅድመ-መሥፈርቶች፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር ተመሥርተው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት ስለሚፈልጉ ተቋማት ስለ ሃይማኖት ተቋማት ስያሜና የዓርማ አጠቃቀም ይናገራል፡፡ የረቂቅ መመሪያው አንቀጽ 5 የሃይማኖት ተቋም ስለ ‹‹መመሥረት›› ይናገራል፡፡ ይህንን የረቂቅ መመሪያውን አንቀጽ ስንመለከተው መመሪያው አዲስ ለሚመሠረቱ የሃይማኖት ተቋማት እንጅ እስከ አሁን ድረስ በሕግ እውቅና ተሰጥቷቸው ወይም ተመዝግበው ያሉ የሃይማኖት ተቋማትን መመሪያው አይመለከታቸውም ማለት ነው፡፡ አንቀጽ 5 ብቻ ሳይሆን የረቂቅ መመሪያው ክፍል ሁለት በሙሉ (ማለትም ከአንቀጽ 5-14 ድረስ) አዲስ ለሚመሠረቱ የሃይማኖት ተቋማት እንጅ ከአሁን በፊት ያሉትን የሃይማኖት ተቋማት አይመለከትም፡፡ አንቀጽ 5 የመንደርደሪያ አንቀጽ ስለሆነ፣ ከዚያ በኋላ ያሉት አንቀጾችም ይህንን ተከትለው የሚሄዱ ስለሆነ፣ የሚናገሩት ስለ ምሥረታና ምሥረታን ተከትሎ ስለሚመጡ ጉዳዮች ነው፡፡ ለዚህም ነው የረቂቅ መመሪያው ክፍል ሁለት በአጠቃላይ፣ ቀድመው በሕግ እውቅና ተሰጥቷቸው ወይም ተመዝግበው ያሉ የሃይማኖት ተቋማትን አይመለከትም የምለው፡፡

አንቀጽ 5 በተለይ እና ክፍል ሁለት ደግሞ በአጠቃላይ ከዚህ ረቂቅ መመሪያ በፊት የሰውነት መብት በሕግም ሆነ በምዝገባ ስላላቸው የሃይማኖት ተቋማት የሚደነግግ ቢሆን ኖሮ፣ ረቂቅ መመሪያው የተለያዩ የሕግ ክፍሎችን፣ መርሆችን እና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ይጥስ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በክፍል 2 ሥር አንቀጽ 5 እና ከዚያ በኋላ ያሉት አንቀጾች በዚህ መልኩ ሊተረጎሙ የሚችሉ ቢሆንም፣ ይህ አተረጓጎም ግን የሚያስተማምን እና ዘለቄታ ያለው አይመስልም፡፡ በርግጥ በሕግ አተረጓጎም መሠረት፣ ክፍል 2 በተለይም አንቀጽ 5 ቀድሞ የነበሩ የሃይማኖት ተቋማትን እንደማይመለከት ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም አንቀጽ 5 በግልጽ የሚደነግገው ስለ ምሥረታ ነው እንጅ ቀድመው ስላሉ የሃይማኖት ተቋማት ምሥረታ አይደለምና ነው፡፡ ሕጉ ግልጽ ከሆነ ደግሞ ምንም ዓይነት ትርጉም ስለማያስፈልገው፣ ክፍል 2 ቀድመው የነበሩ የሃይማኖት ተቋማትን አይመለከትም፡፡

ነገር ግን ክፍል 2 እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ ድንጋጌ አይመስልም፡፡ ለዚህም በረቂቅ መመሪያው የመሸጋገሪያ ድንጋጌ (አንቀጽ 36) ላይ ቀድመው ስላሉ (የሕግ ሰውነት ስላላቸው) የሃይማኖት ተቋማት ይደነግጋል፡፡ ይህ አንቀጽ ‹‹ቀደም ሲል በሌላ አካል ‹‹ተመዝግበው›› ሥራ ላይ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት መመሪያው ከጸናበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ በመመሪያው መሠረት እንቅስቃሴያቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡›› በማለት ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ ይህ አንቀጽ ከዐረፍተ ነገር አወቃቀሩ ጀምሮ እጅግ በርካታ ችግሮችን ያዘለ፣ ለትርጉም ደግሞ እጅግ የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ከአሁን ቀደም ያለውን አሰራር በሙሉ ፈራሽ የሚያደርግ ነው፤ በሕገ-መንግሥት፣ በአዋጅም ሆነ በደንብ የተቀመጡ ነገሮችን፣ መርሆችን የሚጥስ ሊሆን ነው፡፡ ትንሹ ትልቁን ሊያፈርስ ነው ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም እስኪ እያንዳንዱን የአንቀጹን ነገር በተናጥል እንመርምረው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ አንቀጹ ከአሁን በፊት ‹‹ተመዝግበው›› ስላሉ የሃይማኖት ተቋማት ነው የሚናገረው፤ ከላይ እንደጠቀስኩት ደግሞ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በምዝገባ አይደለም የሕግ ሰውነትን ያገኙት፡፡ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን የሕግ ሰውነትን ያገኘችው በምዝገባ ሳይሆን ሕግ የሰውነት መብት እንዳላት እውቅና የሚሰጣት፡፡ ስለዚህም ይህ መሸጋገሪያ ድንጋጌ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያንን አይመለከትም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ይህ አንቀጽ (36) ከአንቀጽ 5 ጋር ይጋጫል፡፡ ከላይ እንደተመለከተው አንቀጽ 5 ከአሁን ቀደም ያሉትን የሃይማኖት ተቋማት አይመለከትም፡፡ ይህ ማለት ከአሁን ቀደም ያሉት የሃይማኖት ተቋማት በአንቀጽ 5 መሠረት አዲስ ምሥረታ እንደማያስፈልጋቸው አይተናል፡፡ አንቀጽ 36 የመጨረሻው ሀረግ ‹‹…በመመሪያው መሠረት እንቅስቃሴያቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡›› የሚል አለው፡፡ ቀደም ያሉት የሃይማኖት ተቋማት ‹‹… በመመሪያው መሠረት እንቅስቃሴያቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ ማለት ቀደም ያሉት የሃይማኖት ተቋማት እንደገና ይመዘገባሉ፣ የሃይማኖቱ ስያሜ፣ ዓርማ፣ አጠቃቀሙ እንደገና በመመሪው መሠረት ይስተካከል ማለቱ ነው? እነዚህ ቀደም ባለው ሕግ የሰውነት መብት ያላቸው የሃይማኖት ተቋማት በአንቀጽ 36 መሠረት እንደገና ይመዝገቡ የምንል ከሆነ፣ አንቀጽ 5 መሠረት የቀደሙትን የሃይማኖት ተቋማት እንደገና ምሥረታ አያስፈልጋቸውም ካልነው ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አንቀጽ 36 ከላይ በተቀመጠው መልኩ የሚሆን ከሆነ፣ ቀደም ብለው የሕግ ሰውነት መብት ያላቸው የሃይማኖት ተቋማት መብትና ግዴታቸው እንደገና ይወሰናል ማለት ነው? እንዲያው በአጠቃላይ ሁሉንም ነገር በመመሪያው መሠረት ‹ሀ› ብለው ሊጀምሩ ነው ማለት ነው? ይህ ማለት እኮ እንደገና ከዜሮ እንጀምር ማለት ነው! እነደዚህ ማለት ደግሞ ከአሁን በፊት ያለውን አሠራር ውድቅ፣ በሕግ ቋንቋ ‹‹ዋጋ አልባ/Void››፣ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ከሕገ-መንግሥቱ ጀምሮ ሃይማኖትን የሚመለከቱ አዋጆችንና ደንቦችን ሁሉም፣ በተዋረዱ ትንሽ በሆነ ሕግ (መመሪያ) ሊሻሩ ነው ማለት ነው፡፡ የማይሆን ነገር ነው-በሕግ ዘንድ!

ውድ አንባቢያን፣ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚፈጠር ግጭትን ስለመፍታት፣ ስለ አስተዳደር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሕገ-መንግሥቱና ከሌሎች የሀገሪቱ ሕጎች ጋር በማገናዘብ ለመመርመር በሚቀጥለው ክፍል እመለሳለሁ፡፡ እስከዚያው ደህና እንሁን!


[1] የሕግ ተዋረድ የሚባለው እንዲህ ነው፤ ከላይ ሕገ-መንግሥት (Constitution) አለ፤ ከዚያም አዋጅ (Proclamation)፤ ከዚያ ቀጥሎ ደንብ (Regulation)፤ ከዚያ ቀጥሎ መመሪያ (Directive)፤ ከዚያ ቀጥሎ የሕግ ክፍል ማስታወቂያ (Notice)፤ … ከዚያም በሕግ ተዋረድ የመጨረሻ እስከሆኑት (bye-laws) ይደርሳል፡፡ እነዚህ ሁሉም ሕግ ተብለው ይጠራሉ፡፡

 

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s