ስለ ሽምግልና፤

ሽምግልና በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው እሴቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሽምግልና አለመግባባቶችን፣ ልዩነቶችን፣ ቅራኔዎችን ለመፍታት የሚያስችል ትልቅ ሃብት ነው፡፡ ሽምግልና የትኛውንም ዓይነት ጥፋት፣ አለመግባባት፣ ጠብ፣… በተጣሉት ወገኖች መካከል ምንም ቅሬታ ሳይኖር ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ታልቅ ተቋም ነው፡፡ በቀድሞው ዘመን ሰው ከሰው ጋር፣ ከመንግሥት ጋር፣ መንግሥት ከመንግሥት ጋር ቢጋጩ ነገሩ በሽምግልና የሚያልቅበት አግባብ ነበር፡፡ ሽምግልናን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ ሸምጋዮች ዕድሜና ጾታ፣ ደረጃና ሥራ፣ ሳይለያቸው ሁሉም ሰው ሊሳተፍበት የሚችል መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ማንኛውም ሰው ለሽምግልና ብቁ ነው፤ የዕድሜ፣ የሥልጣን፣ ነጭ ፀጉር የማብቀል፣ የሃብት፣ የአንቱታ፣ የሌሎችም ሰዋዊ መመዘኛዎች ጉዳይ አይደለም-ሽምግልና፡፡ ለሸምጋይነት የሚያበቃ ሰብአዊነት ባለቤት መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ችግርን/አለመግባባትን የመረዳት፣ የሚዛናዊነት፣ የበጎ ኅሊና ባለቤትነት፣ የኢ-ወገንተኝነት/አለማዳላት፣ ጉዳይ ነው-ሽምግልና፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሽምግልና ሁሉንም ዓይነት አለመግባባቶች ለመፍታት የሚያስችል፣ ተቀባይነቱ በተሸምጋዮች ዘንድ የታወቀ፣ የታፈረና የተከበረ ሥርዓት ነው፡፡ በሽምግልና መፍትሔ የሌለው ችግር አይኖርም፤ የቀማ፣ የካደ፣ ያጠፋ፣ የሰረቀ፣ ሚስቱን፣ ልጁን፣ ወላጁን የበደለ፣ አልጋ ለመነቅነቅ ያሰበ፣ የሸፈተ፣ ያመጸ፣ የገደለ፣ ቃሉን የበላ፣ …. እረ ስንቱ … ሁሉም በሽምግልና ያልቃሉ፡፡ ሽምግልና የማይፈታው ቋጠሮ፣ የማይሽረው በደል፣ የማያክመው ጠባሳ፣ የለም፤ ለሽምግልና እጁን የማይሰጥ፣ የማይንበረከክ፣ አክብሮት የሌለው …. ሰው የለም፡፡ (ይህም ከሽምግልና ጀርባ ይቅርታ ስላለ ነው፤ ዋናው ርዕሰ-ጉዳይዬ ይቅርታ ስላልሆነ ወደ ቀደመው ነገሬ ልመለስ፡፡) ሽምግልና ቀድሞም ያለ፣ አሁንም ያለ፣ ወደ ፊትም የሚኖር ትልቅ ሃብት ነው፡፡ በሽምግልና፣ ለፍ/ቤት ዳኝነት እንደሚከፈል ክፍያ የለም፤ ሽምግልና እንዲሁ ከበጎነትና ከቅንነት የመነጨ በጎ ተግባር እንጅ ንግድ አይደለም (በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በታች ሰፋ አድርጌ ለማየት እሞክራለሁ-ዋናው የመነሻ ሃሳቤም ይኼው ስለሆነ)፡፡ ታዲያ እንዲህ ስል በተሸምጋዮች መካከል ያለው ጉዳይ /ማለቴ አለመግባባት/ በሽምግልና ከተቋጨ በኋላ ስለ ፍቅር ብለው የሚበሉትንና የሚጠጡትን ‹ፍንጥር› (‹ጥ› አትጠብቅም)  ዘንግቼው እንዳይመስላችሁ፡፡ እንዲያውም ‹ፍንጥር› የሽምግልናው አንዱ አካል ናት፡፡ [ወይም በኢህአዴግ ቋንቋ ‹ተሃድሶ› የሚባለው ዓይነት፤ በርግጥ በኢህአዴግ ዘንድ ‹ተሃድሶ› የሚደረገው አብዛኛውን ጊዜ ስብሰባ/ሥልጠና ከተካሄደ በኋላ ለተሰብሳቢዎች የሚቀርብ የ‹እንኳን ስብሰባው/ሥልጠናው ተጠናቀቀ› የመብልና የመጠጥ ዝክር ነው፡፡] ለማንኛውም ‹ፍንጥር› ስሙ ይለያይ እንጅ በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡

ይህም በመሆኑ ሽምግልና በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ በሕግ ውስጥ እንዲካተት ከተደረገ ቆይቷል፡፡ በሌሎች አገሮችማ ሽምግልናን ወደ ሕጋቸው ውስጥ ካካተቱት ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ለነገሩ በኛም አገር ቢሆን ሕግን በጽሑፍ መልክ ማድረግ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በመሆኑ ነው እንጅ ቀድሞውንም ነገሥታት የአዋጃቸው አካል አድርገውት ነበር፤ የበደልክ ግባና ታረቅ፣ ያመጽኽ ገብርና/ታረቅና ግዛትህ ይመረቅልሃል እያሉ ሲሰሩበት የነበረ ነው፡፡ ታዲያ ዘመናዊ የመንግሥት ሥርዓት ከተጀመረ ወዲህ ሽምግልና ምንም እንኳ አስፈላጊነቱና ተቀባይነቱ እንዳለ ቢሆንም በአንዳንድ የመንግሥት ጉዳዮች ላይ ግን እንዳይደርስ ተከልክሏል-ለዚያውም በግልጽ ሕግ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ሽምግልና በወንጀል ጉዳዮች ላይ እጁን እንዳይሰድ ተደርጓል፡፡ በሽማግሌ ታርቄአለሁና ልጠየቅ አይገባኝም ብሎ መከራከር ከቀረ ቆይቷል፡፡ በርግጥ በአንዳንድ የወንጀል ጉዳዮች ሽምግልና እስከአሁንም ድረስ አገልግሎት መስጠቱ አልተጓደለበትም፡፡ ይኼንን እንተወውና ሰፊው ሕዝብ ‘ኮ (በተለይም ከፍ/ቤቶች ርቆ የሚኖረው ወገናችን) እስከ አሁን ድረስ ወንጀልን በሽምግልና ነው የሚቀጨው፡፡ ፍ/ቤቶቹስ ቢሆኑ፣ ሕጉ ሽምግልናን ገፋ ያደረገው ቢመስልም፣ እነሱ ግን እስከአሁን ከጎናቸው እንዳሰለፉት አይደል እንዴ፡፡ ከወንጀል ጉዳዮች ባሻገር በሌሎች መንግሥትን በሚመለከቱ ወይም የመንግሥት ጥቅም ባለባቸው ጉዳዮችም ሽምግልና እንደተከለከለ ነው፡፡ (እዚህ ላይ መንግሥት ስል በተለይ በአሁኑ ዘመን ‹ሕዝብ› ማለቴ እንደሆነ ይሰመርልኝማ፡፡)     

በዘመናዊው ዓለም ውስጥ በተለይም በሕግጋቱ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት የሽምግልና ዘዴዎች አሉ፡፡ እኔም ስሙ፣ ታሪኩ፣ አገልግሎቱና ሽፋኑ ሰፋ ብሎ ስለታየኝ እንጅ ይህንን ዘንግቼው አይደለም፡፡ ከሽምግልና በተጨማሪ እርቅ፣ ግልግል፣ ድርድር፣ …. የሚሉ ተቀራራቢ፣ ግን የተወሰኑ ልዩነቶች፣ ግን ደግሞ አንድ ዓይነት ዓላማ ያላቸው ሥርዓቶች/እሴቶች እንዳሉ ልብ ይሏል፡፡ በተለይም ግልግልና ድርድር የሚባሉት በዘመናዊ ትርጉማቸው በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ የተለመዱ ናቸው፡፡ ሽምግልና ደግሞ በቤተሰብ/ጋብቻ፣ ውርስ፣ ንብረት፣ እና ሌሎች ግላዊ ግንኙነትን በሚመለከቱ ዘርፎች የሚዘወተር ቃል ነው፡፡ በዚህች ትንሽ ዲስኩሬ ሽምግልና የሚለውን ቃል የግል ግንኙነቶችን በተመለከተ ስለሚደረገው የግጭት መፍቻ፣ ግልግል የሚለውን ደግሞ ለንግድ ግንኙነቶች ስል ተጠቅሜያለሁ፡፡

ለሽምግልና የሚከፈል ክፍያ እንደሌለ ከላይ ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ አለመግባባቱ፣ የተሸምጋዮችም፣ የሸምጋዮችም ደረጃ ከፍ ያለ ቢሆን ሽምግልና ዋጋ አይጠየቅበትም፡፡ በአንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም “አገቱኒ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 105 ላይ ስለ ሽምግልና እንዲህ አሉ፤ “….ሽምግልና ዋጋ የሚከፈልበት ሲሆን ይረክሳል፤ ወደ ሸቀጥነትም ይወርዳል፤ ሸምጋዮቹንም፣ ተሸምጋዮቹንም ያዋርዳል፡፡…. በርግጥ እርሳቸው እነደዚህ ያለውን አባባል በምን ዐውድ እንደተናገሩት ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡ ፕ/ር እንዲህ ያሉበት ምክንያት እርሳቸውና ሌሎች ጓደኞቻቸው ምርጫ ‘97ን ተከትሎ ‹በአልጋ ንቅነቃ› እና በሌሎችም ተጨማሪ ክሶች ተፈርዶባቸው ወኅኒ ከወረዱ በኋላ እነርሱን ለማስፈታት ስለተደረገው የሽምግልና ጉዞ ሲተርኩልን ነው፡፡ ስለዚህ እርሳቸው ሽምግልናን ከላይ በተጠቀሰው መልክ ሲገልጹት በወቅቱ ከእስረኞቹና ከመንግሥት ጋር ከነበረው ነገር ጋር ቀጥታ ስለሚያያዝ የሕዝብ-መንግሥት ሽምግልና ነው ማለት ይቻላል፡፡ (እንደ እርሳቸው አገላለጽ ፖለቲካዊ ሽምግልና መሆኑ ነው፡፡) አዎ! በእንደዚህ ዓይነት ሽምግልና ገንዘብ ጣልቃ መግባት የለበትም፤ እንደዚያ ሲሆን ሸቀጥ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጅ የርሳቸው አገላለጽ በጠቅላላው ስለ ሽምግልና ነው (የሚመስለው)፡፡ ይህንንም የምንረዳው፣ በመጀመሪያ ደረጃ እርሳቸው በተለምዶአዊ የጽሑፍ ፍሰት ስለ ሽምግልና ጠቅላላ ነገር ተናግረው ሲያበቃ ነው የዚያን ወቅት የሽምግልና ጉዞና ታሪክ የሚነግሩን፡፡ ሁለተኛም አውሮጳውያንና አሜሪካውያን ሽምግልናን የሚያዩበትን ዐይንና ስለ ሽምግልና ያላቸውን ተግባር በአንዲት አጭር ዐረፍተ-ነገር ይነግሩናል፡፡ በዚህም መሠረት እርሳቸው የኮነኑት ገንዘብ የሚከፈልበትን ሁሉንም ዓይነት ሽምግልና ይመስላል፡፡

ፕ/ሩ ሽምግልናን የገለጡበት ነገር ምን ዓይነት ድርጊት ሽምግልናን ሊያወርደው እንደሚችልና ለታላቁ የሽምግልና እሴትነት ያላቸውን ትልቅ አክብሮት ያሳየናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በተለይም በአሁኑ ዘመን ያለውን የሽምግልና ነገር ገላልጠን ብናየው እርሳቸው ምን ይሉ ይሆን? አይ …. ለጊዜው መገመቱን ልተወውና ሽምግልና በአሁኑ ዘመን እንዴት ያለ ሚና እንዳለውና እርሳቸውን ስለሚከብዳቸው ‹የሽምግልና ንግድነት› እንመልከት፡፡ በዋናነት ትኩረቴን ቤተሰብንና ንግድን ስለሚመለከቱ ሽምግልናዎች ዙሪያ አደርጋለሁ፡፡ 

ሽምግልና በርግጥም ንግድ ሲሆን ይረክሳል፡፡ ለዚህም አንድ አብነት እንመልከት፡፡ የቤተሰብ ጉዳይ በነባሩ ባሕልም ሆነ በዘመናዊ ባሕል በሽምግልና ከሚታዩ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ እንዲያውም የቤተሰብ/ትዳር ጉዳይ ከሌሎች ጉዳዮች ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንደኛው በጣም ግላዊ መሆኑ ነው፤ ይህ ማለት የቤተሰብ ነገር የባልና የሚስቱ ጉዳይ ነው፤ የቤታቸውን ጣጣ አደባባይ ማዋል የቤተሰብን ምሥጢር/ገመና ለህዝብ ገበያ እንደማዋል ነው፡፡ ለዚህም ነው የቤተሰብ ጉዳይ ብዙውን ጊዜ ልማዱም፣ ሕጉም በቤተ-ዘመድ ሽምግልና ማለቅ አለበት ብሎ የሚደነግገው፡፡ በቤተሰብ መሀል በተለይም ትዳርን/ጋብቻን በተመለከተ አለመስማማት ቢኖር ሕጉም እንደሚለው በሽምግልና ማለቅ አለበት፡፡ ታዲያ ይህ ነገር ቀደም ባለው ዘመን አሁንም ድረስ በቤተ-ዘመድ ጉባኤ/ሽምግልና ሲዳኝ ኖሯል፡፡ በዘመናችን ደግሞ በተለይ በከተሜው ዘንድ የቤተሰብ ሽምግልና ከነዋሪው ባህል ሾልኮ ያፈነገጠ ይመስላል፡፡ አቶ መሓሪ ረዳኢ ስለ ፌዴራሉ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ሲያብራሩ ሽምግልናን ሞያ/መተዳደሪያ/ አድርገው የያዙ፣ በሸምጋይነታቸው ክፍያ የሚከፈላቸው፣ አንዳንድ ጊዜም ከሽምግልናው መራዘም ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ሽምግልናን ከሚጠበቀው በላይ የሚያጓትቱ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ እንግዲህ ፕ/ር መሥፍን የተናገሩትን ከዚህ ላይ ብናነሳው አግባብ ይሆናል፡፡ ሽምግልና ለዚያውም የቤተሰብ/ትዳር ጉዳይ በተከፋይ ሽማግሌዎች እንደሚዳኝ ቢሰሙ ባሕር ማዶ አሜሪካንንና አውሮጳን መጥቀስ ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ አቶ መሓሪ እንደጠቀሱት አይነት ሽምግልና በርግጥም ፕ/ሩ እንደተናገሩት ሽምግልናን ያረክሳል፤ ሸቀጥም ይሆናል፡፡    

እስኪ ደግሞ ወደ ንግድ-ነክ አለመግባባቶች ልመልሳችሁ፡፡ የንግድ ዓይነቶችም እንደ መሸጥ፣ መለወጥ፣ የንግድ ማኅበር በማቋቋም መሥራት፣ በማምረት ሥራ መሠማራት፣ ንዋይ በማፍሰስ/Investment/፣ በባንክ፣ በመድን፣ እና የመሳሰሉትን የሥራ ዘርፎች ያካትታል፡፡ በንግድ ሥራ ውስጥ አለመግባባት፣ እንደ ቃል አለመገኘት፣ ውል ማፍረስ፣ እና ሌሎችም ስላሉ አነዚህን እልባት መስጠትም አብሮ የሚሄድ ነገር ነው፡፡ እንደ ሽምግልና ሁሉ በተለይ ለንግድ ጉዳዮች ደግሞ ‹ግልግል› አለመግባባቶችን ለመፍታት ሁነኛ ዘዴ ነው፡፡ እንዲያውም የንግድ አለመግባባቶች ግልግል፣ ከቤተሰብ ሽምግልና ከፍ ብሎ ዓይነቱም መንገዱም ሰፋ ብሎ እናገኘዋለን፡፡

አሁንም አስቀድመን የገንዘብን/ክፍያን ነገር እናንሳ፡፡ የዘመናችን የቤተሰብ ጉዳዮች ሸምጋዮች ክፍያ እንደሚጠይቁት ሁሉ የንግድ ጉዳዮችን የሚያገላግሉ ገላጋዮችም ጠቀም ያለ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ እንዲያውም ይግረማችሁ፣ የንግድ አለመግባባቶች ክርክርን መገላገል ንግድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ፕ/ር መሥፍን አሜሪካንንና አውሮጳን የጠቀሱት የንግድ ሥራ አለመግባባት ግልግሎችን መሆን አለበት፤ በነዚህ ክፍለ-ዓለማት ይህ ሥራ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እናየዋልን፡፡ በገንዘብ ደረጃ እጀግ በጣም ትልልቅ ጉዳዮችን ነው የሚያገላግሉት፤ በርካታ፣ የሠለጠነ፣ ከፍተኛ ልምድ ያለው የሰው ሃይል፣ የሕግ ሽፋን አላቸው፡፡ በሃገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ውጥን ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የንግድ ግልግል ምንም እንኳ ያን ያኽል የዳበረ ባይሆንም እየተከፈላቸው የንግድ አለመግባባቶችን የሚገላግሉ አሉ፡፡ ለገንዘብ የሚደረግ ሥራ ነው!

ሁለተኛው የንግድ ግልግልን ከቤተሰብ ሽምግልና ይልቅ ልዩ የሚያደርገው የግልግል ተቋማት በሕግ ወይም በማኅበር መቋቋማቸው ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን የገላጋይ ተቋማት በአዋጅ ያቋቁማል፤ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ‘ኮ በ1995 በአዋጅ የተቋቋመ የግልግል መድረክ ነው፡፡ ሕግ ተቀርጾለት፣ ጽሕፈት-ቤት ተቋቁሞለት፣ በጀት ፈሰሰ ተደርጎለት፣ የሰው ሃይል ተቀጥሮለት፣ የሚሠራ የንግድ ጉዳዮች የግልግል መድረክ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱም የከተማ መስተዳድሮች ዘንድ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት የተባሉት የንግድ ጉዳዮች የግልግል ተቋማት ተቋቁመዋል፡፡ ደግሞ ይህ በ1995 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመ እንዳይመስላችሁ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1935 ዓ.ም ነው የዚህ መሠረቱ የተጣለው፡፡ መቼ በዚህ ብቻ ያበቃና፤ ማኅበር በመመሥረት የንግድ ጉዳዮችን ለመገላገል የተቋቋመ ነበረ- ‹የኢትዮጵያ የእርቅና የግልግል ማዕከል› የሚባል (ሞተ እንጅ)፡፡ ይህ ተቋም ለሚሰጠው የግልግል ሥራ ገንዘብ እየተከፈለው ይሠራ ነበር፡፡ የበጎ አድራጎት ማኅበራትና ድርጅቶች አዋጅን አይከተለም ተብሎ በቅርቡ ፈረሰ አሉ፡፡

እንግዲህ ድርሞዬን ልንገራችሁ፡፡ ሽምግልና ቀድሞም ያለ፣ አሁንም ያለ፣ ወደ ፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ እንደ አለመግባባቱ ሁኔታ ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ቀድሞ ዘመን ሽምግልና እንደ ማኅበራዊ ግዴታ የሚታይ ነበር፤ በቅንነትና ያለ ዋጋ የሚሠራ ነበር፡፡ በርግጥ አሁንም ይኼ ነገር እንዳለ ቢሆንም ገንዘብ እየተጠየቀበት መጥቷል፡፡ በጣም በሚከበረውና ግላዊ በሚባለው በቤተሰብ ጉዳይ እንኳ ገንዘብ የሚከፈልበት ‹ሸቀጥ› ሆኗል፤ ታዲያ ክብሩም ሳይቀነስ አልቀረም፡፡ ንግድን በተመለከተማ በተለይ ሽምግልናና መገላገል ‹ንግድ› ሆኗል፡፡ በርግጥ የቤተሰብን ሽምግልና ስንመለከት ‹ተሸረሸረ› ማለታችን አይቀርም፡፡ የሚጠፋ እንኳ አይመስልም፡፡ በተለይ በንግዱ በኩል ያለው ግን እንዲያውም ወደ ፊት ከዛሬው በበለጠ የሚፋፋ ይመስለኛል፡፡

Advertisements

One thought on “ስለ ሽምግልና፤

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s