ቤተ-መጻሕፍት፣ ቤቱና ሕግጋቱ

የቤተ-መጻሕፍት ነገር ሲነሳ ምን ትዝ ይላችኋል? ማለቴ ሕግጋቱን በተመለከተ? ጸጥታ! የሚለው በአንክሮ የተጻፈ ጽሑፍ፣ አመልካች/ሌባ ጣቷን ከአፏ ላይ ያስቀመጠች ስዕል፣…. የማያስተውስ መቼም አይኖርም፣ ቤተ-መጻሕፍት ገብቶ የማያውቅ ካልሆነ በቀር፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ በቀይ ቀለም የተጻፈ X ያለበት የሞባይል ስዕል፡፡ በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለን እነዚህን የቤተ-መጻሕፍት ሕግጋት የማይፈራና የማያከብር ተማሪ ካለ ቅጣት ለመቀበል የፈቀደ መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ የሚያስቁ ነገሮች እንኳ ቢያጋጥሙ በልብ ወይንም አፍን በመዳፍ አፍኖ ካልሆነ በቀር አይታሰብም፡፡ መነጋገርና ማውራትማ ፈጥሞ የተወገዘ ነው፤ ምናልባት ቢኖርም እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ መንሾካሾክ፡፡

ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ላይም ይህ የቤተ-መጻሕፍት ሕግ የታወቀ፣ የሚከበር ነው፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ፡፡ በአጠቃላይ ጸጥታ! የትም ቢኬድ፣ የትም ቢደረስ፣ ማንም ምንም ቢሆን የቤተ-መጻሕፍት የማትሻር፣ የማትቀር ሕግ ናት፡፡ ሁሉንም ትገዛለች፤ ዕድሜ፣ ጾታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ማንነት/status/ አትለይም፡፡ ግልጽ የሆነች፣ እጅግ ደስ የምትል፣ አስገራሚ ሕግ፣ ጸጥታ!

ተማሪ ግን በትምህርት፣ በእዉቀት ከፍ ሲል ሕግ አለማክበሩም፣ ትእቢቱም፣ ንቀቱም አልፎ አልፎም ድንቁርናው ከፍ ስለሚል ጸጥታ የምትለው ሕግ ትረሳለች፣ እየታወቀችም ትሻራለች፡፡ በትምሕርት ከፍ ባሉ ሰዎች ዘንድ ትዘነጋለች፡፡

አሁን በምማርበት ዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተ-መጻሕፍት ለመሄድ ሳስብ አስቀድሞ የሚታወሰኝ የጸጥታው ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ለቤተ-መጻሕፍት ያለኝ ግንዛቤና አክብሮት /ለሕጉ/ አሁን በጣም ተለያይቷል፡፡ የቤተ-መጻሕፍት ጸጥታ ይናፍቀኛል፣ አርምሞው ይርቀኛል፡፡ በተለይ ስልክ የሚባል ነገር ጣልቃ ከገባ ወዲህ ቤተ-መጻሕፍትን ጸጥታ የራቀው ይመስለኛል፡፡ እንዳንድ ጊዜ ጸጥታ ያለበትን ቤተ-መጻሕፍት ፍለጋ እዚያም እዚህም እላለሁ፤ ግን ሁሉም ያው ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የድሕረ-ምረቃ ተማሪዎች ቤተ-መጻሕፍት ለቅል ነው፡፡ ኬኔዲ ቤተ-መጻሕፍትን እምምምምም…….፣ እዝዝዝዝዝ…….፣ የሚለው ድምጽ ተቆጣጥሮታል፡፡ በተለይ ኬኔዲ የቅቤ ገበያ ነው የሚመስለው፡፡ ዛሬስ አኔም ተመርሬ ከዚያ መሄዱን ትቼዋለሁ፡፡

ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ስልክን ድምጽ አልባ/silent/ ማድረግ ያስቀጣል የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ ስልክን መዝጋትማ ዘበት ነው፡፡ ታዲያ የስልክ ጥሪዎች በሁሉም አቅጣጫዎች ሲጮሁ ቤቱን ቤተ-መጻሕፍት ሳይሆን የሙዚቃ ቤት ያስመስለዋል፡፡ ስልክ ሲነሳ ደግሞ ልክ ከቤት ውጭ ያለ ነው የሚያስመስለው፤ ጉሮሮን ሙሉ በሙሉ ከፍቶ ማውራት ነው..… ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የማየውን እኮ ነው የማወራላችሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ረዘም ያለ ንግግር ይደረጋል፡፡ በቃ ምን አደከማችሁ….በስልክ ማውራት የተፈቀደ ነው የሚመስለው፡፡ ስልክ ከቤተ-መጻሕፍቱ ውጭ ወጥተው የሚያናግሩ ጨዋ ሰዎች መኖራቸው ግን አይዘነጋም፡፡ ቤተ-መጻሕፍቱ ውስጥ ከማውራት፣ ለምን አጭር የጽሑፍ መልእክት በመላክ የቤተ-መጻሕፍቱን ሰላም አንመልስም? አማራጭ መንገድ እያለ አለመጠቀም ትእቢት ወይም ንቀት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ወንበር ሲንቀሳቀስ ወይም ሲጎተት የሚያዋጣው ድምጽ ደግሞ የበለጠ የሚረብሽ ነው፤ ሲጢጢጢጢ…. ሲል ውስጥን የሚያሳቅቅ….. ረባሽ ድምጽ፣…….፡፡ ወንበሮችን ቀስ አድርጎ በማንሳት መነሳት ወይም መቀመጥ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ ወንበር ሲጎተት አስቀያሚ ድምጽ ስለሚያወጣ ብድግ አድርጎ ማንሳቱ መፍትሔ ነው፡፡ በቃ አለቀ….፡፡

ደግሞ ቤተ-መጻሕፍቱ ውስጥ የማንበቢያ ሳጥኖች አሉላችሁ፤ እነዚያ ውስጥ ነጻነት እስከ አፍንጫው ነው፡፡ ይዘጋሉ፤ ወግና ቀልድ ከዚያ ይወራሉ፤ የክፍል ሥራና የቤት ሥራ ከዚያ የሚሠራ ነው የሚመስላችሁ፡፡ መንሾካሾኩንማ ተዉት፣ አይወራ ይቅር፡፡

በአጠቃላይ የቤተ-መጻሕፍት ሕጉ፣ ጸጥታ ክልክል ነው! የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ ጣቷን ከአፏ ላይ ያስቀመጠችው ስዕልም ጣቷን ሳታነሳው አልቀረችም፡፡ የሞባይል ስዕሏ ደግሞ የX ምልክቱ ሳይፋቅላት አልቀረም፡፡ አቦ ቤተ-መጻሕፍት መሆኑን እናስብ እንጅ፤ ለሌላው ተማሪም እናስብ፡፡ ወይስ ደግሞ ዛሬም ጸጥታ ይከበር! የሚለው ማስጠንቀቂያ ይለጠፍልን!?

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s